ኢሳት (የካቲት 21 ፥ 2009)
በመገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ የሃይል ማመንጫ አቅሙ በ450 ሜጋ ዋት እንዲያድግ ተደርጓል መባሉ በግብፅ በኩል ስጋት ማሳደሩን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ማከሰኞ ዘገቡ።
ሰሞኑን የኮሚኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶር ደብረጽዮን ገብረሚካዔል በግድቡ ላይ በተደረገ ማሻሻያ 6ሺ ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ያቀርባል ተብሎ የነበረው ግድቡ ወደ 6450 ሜጋዋት ከፍ ማለቱን መግለጻቸው ይታወሳል።
ይሁንና የግብፅ የውሃ ምህንድስና ባለሙያዎች ፖለቲከኞች ሃገሪቱ የወሰደችው ዕርምጃ የወንዙን ፍሰት ይቀንሳል የሚል ስጋት ማጫሩን ማዳ ማስር የተሰኘ ጋዜጣ አስነብቧል።
የተለያዩ የግብፅ ምሁራን የግድቡ ሃይል ማመንጫ አቅም ከፍ ማለቱ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በመተንተን በመንግስታዊ ጋዜጣ አልሃራም እትም የተለያዩ ጽሁፎችን ማቅረባቸውንም ጋዜጣው አክሎ አመልክቷል።
መስታፍ አልፈኪ የተባሉ ምሁር የግድቡ ግንባታ አቅም አድጓል መባል በግብፅ የውሃ ድርሻ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን አስነብበዋል።
የግብፅ መንግስት ግንባታው በመካሄድ ላይ ያለው የአባይ ግድብ የአባይ ወንዝ ፍሰትን ይቀንሳል በሚል ስጋቱን ሲገልፅ መቆየቱ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ግድቡ አቅሙ በድጋሚ ከፍ እንዲል ተደርጎ 6450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያመነጭ ከቀናት በፊት ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ ዕርምጃው በሁለቱ ሃገራት መካከል አዲስ አለመግባባት ሊቀሰቅስ እንደሚችል የግብፅ ምሁራት በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ማዳ ማስር ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
ግድቡ የሃይል ማመንጨት አቅሙ ከፍ እንዲል ማድረጉን ያሳወቁት የመንግስት ባለስልጣናት ከግብፅ በመቅረብ ላይ ስላለው አዲስ ስጋት የሰጡት ምላሽ የለም።
የአባይ ግድት ተጨማሪ 450 ሚጋዋት እንዲያመነጭ መደረጉ የግንባታዊ መጠናቀቂያ ጊዜን እንዲሁም በተያዘለት በጀት ላይ ለውጥ ያምጣ አያምጣ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።