ሞ-ኢብራሂም ፋውንዴሽን ለ2016 አም የሚሸልመው አፍሪካዊ መሪ ማጣቱን ገለጸ

ኢሳት (የካቲት 21 ፥ 2009)

በአፍሪካ የመልካም አስተዳደር ዴሞክራሲ እንዲጎለብት አስተዋጽዖን ላደረጉ መሪዎች የአምስት ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ሽልማት የሚሰጠው ሞ-ኢብራሂም ፋውንዴሽን ለሁለተኛ ተከታታይ አመት ለ2016 አም የሚሸልመው መሪ ማጣቱን ማክሰኞ ገለጸ።

በፋውንዴሽኑ የሽልማቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሳሊም አህመድ ሳሊም ለ2016 አም ለሽልማቱ የሚበቁ የቀድሞ የአህጉሪቱ መሪዎችን ለመምረጥ በተደረገ ስራ አንድም መሪ መስፈርቱን ሊያሟላ እንዳልቻለ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለስልጣን የበቁ፣ በህገ መንግስት መሰረተ የስልጣን ዘመናቸው የጠበቁ እንዲሁም እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2014 እስከ 2016 ስልጣን የለቀቁ መሪዎች ለሽልማቱ በዋና መስፈርትነት ተቀምጠው እንደነበር ታውቋል።

ይሁንና ከ54 የአፍሪካ ሃገራት መካከል አንድም የአህጉሪቱ መሪ መስፈርቱን ሳያሟላ መቅረቱን የሞ-ኢብራሂም ፋውንዴሽን ሃላፊዎች ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ ዘግቧል።

በ2009, 2010, 2012, 2015 በተመሳሳይ መልኩ ለሽልማቱ የሚመጥን መሪ ጠፍቶ እንደነበር ያወሳው ፋውንዴሽኑ የአፍሪካ የመልካም አስተዳደር ኣና የዴሞክራዊ ግንባታ አሁንም ድረስ ብዙ መሻሻሎችን የሚፈልግ እንደሆነ አመልክቷል።

የሞዛምቢ ቦስትዋና፣ ኬፕ ቨርድ እና የናሚቢያ የቀድሞ መሪዎች በ10 አመት ውስጥ ሽልማትን ለመውሰድ የበቁ ሲሆን፣ ለስድስት አመታት የ5 ሚሊዮን ዶላሩን ሽልማት ለመቀበል የበቃ መሬ አለመገኘቱን ከፋውንዴሽኑ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

የብሪታኒያ ዜግነት ባላቨው ሱዳናዊው ባለሃብት ሞ-ኢብራሂም የተቋቋመው ይኸው ፋውንዴሽን በአህጉሪቱ ያለው የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ እንዲጎለብት አስተዋጽዖ ለማድረግ በሚል ከ10 አመት በፊት ሽልማቱን ማስተዋወቁ ይታወሳል።

ከ2014 አም ጀምሮ በአህጉሪቱ የታንዛኒያ፣ ጋና፣ ሞዛምቢክና፣ ናይጀሪያ መሪዎች ከስልጣን ቢለቁም አንዳቸውም የፋውንዴሽኑን መስፈርት ሳያሟሉ መቅረታቸውን ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ በሽልማቱ ዙሪያ ባቀረበው ዘገባ አመልክቷል።

የፋውንዴሽኑ የሽልማት አስተባባሪ ኮሚቴ አራቱ መሪዎች በሰላማዊ መንገድ ስልጣንን ቢለቁም መስፈርቱን ሳያሟሉ መቅርታቸውን አክሎ ገልጿል።

ለሽልማቱ ከተቀመጠው የስልጣን ጊዜ የቡርኪናፋሶው የቀድሞ ፕሬዚደንት ብሌስ ኮምፓዎሬ፣ በህዝባዊ ተቃውሞ ከስልጣን የተወገዱ ሲሆን፣ የጋምቢያው መሪም በጎረቤት ሃገራት ጣልቃ ገብነት በሃይል ስልጣን መልቀቃቸው የሚታወስ ነው። የሞ-ኢብራሂም ፋውንዴሽን ጠንካራ ነው የተባለ መስፈርቶችን ያስቀመጠው በተሻለ ሁኔታ አስተዋፅዖን ያበረትከቱ መሪዎችን ለማግኘት ያለመ መሆኑን ፋውንዴሽኑ አክሎ ገልጿል።