ኢሳት (የካቲት 20 ፥ 2009)
የአድዋን ድል በማስመለከት በአሜሪካ ዋሽንግተን በተካሄደው ስነ-ስርዓት ለሃገራቸው አስተዋጽዖ ላደረጉ ኢትዮጵያውያን ሽልማት ተበረከተ። “የዳግማዊ ምኒሊክ ሜዳሊያ” በሚል ስያሜ የተሰጠውን ሽልማት ያገኙ ኮማንደር ጣሰው ደስታ፣ አቶ ኤሊያስ ወንድሙ እንዲሁም አቶ ፈንታሁን ጥሩነህን ጨምሮ 10 ያህል ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሃገር ዜጎች መሆናቸውም ተመልክቷል።
በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜ የካቲቲ 18 ፥ 2009 በዋሽንግተን ዲሲ አርሚ ኒቪ ክለቡ በተካሄደው ስነስርዓት ላይ ተገኝተው የዘውድ ምክርቤትን ወክለው ሽልማቱን ያበረከቱት ልዑል ኤርሚያስ ሳህለ ስላሴ ሲሆኑ፣ በስነስርዓቱ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትም ታስበዋል።
የኢትዮጵያ የመጨረሻ ንጉሰ ነገስት የሆኑት የአጼ ሃይለስላሴ የልጅ ልጅ ከሆኑት ልዑል ኤርሚያስ ሳህለ ስላሴ ሽልማቱን የተቀበሉት ኮማንደር ጣሰው ደስታ፣ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ልዑሉ እነኝህን የቀድሞ ባህር ሃይል አዛጅ አድሚራል ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
የዳግማዊ ምንሊሊክን ሚያዳሊያ የተረከቡት ሌላው ተሸላውሚ የፀሃይ ፕብሊሸር ባለቤት አቶ ኤሊያስ ወንድሙ ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ለትውልድ ለማቆየት በባዕድ ሃገር በሚያደርጉት አስተዋጽዖ መሸለማቸውም ተመልክቷል። የአቶ ኤሊያስ ወንድሙን አስተዋጽዖ ያወሱት ልዑል ኤርሚያስ ሳህለ ስላሴ ታላቅ ኢትዮጵያዊ፣ ታላቅ አፍሪካዊ እንዲሁም ታላቅ አሜሪካዊ ሲሉ አወድሰዋቸዋል።
በአሜሪካ ግዙፍ ቤተመጽሃፍት ላይብራሪ ኦፍ ኮንግሬስ በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ክፍል የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ህትመት ሬፈረንስ ስፔሻሊስት የሆኑት አቶ ፋንታሁን ጥሩነህ በዕለቱ ሽልማቱ ከተበረከተላቸው ኢትዮጵያውያን አንዱ ሆነዋል። በባዕድ ሃገር ለሃገራቸው በሚያደርጉት አስተዋጽዖ ሽልማቱ እንደተበረከተላቸው ተመልክቷል።