የካቲት ፲፯ ( አሥራ ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የዛሬ 9 ዓመት የአባይ ድልድይ እንደገና ሲገነባ የመንግስቱ የመገናኛ ብዙሃን ብዙ ብለዋል። በወቅቱ አገሪቱን ይገዙ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ድልድዩን መርቀው ሲከፍቱ ድልድዩ የጃፖን የጥበብ ደረጃ የታየበት፣ የሁለቱን አገራት ዘላለማዊ ግንኙነት የሚያበስር ነው በማለት አሞካሽተውት ነበር። ድልድዩም አባይ ድልድይ መባሉ ቀርቶ ህዳሱ ድልድይ እንዲባል ተወስኖ ነበር። በጊዜው በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ኪንቺ ኮማኖ ደግሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተሰራው ድልድይ የጃፓንንና የኢትዮጵያን የቆየ ግንኙነት የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ ያለፈውን እና የወደፊቱን ትውልዶች የሚያገናኝ ነው ሲሉ ውዳሴያቸውን ገልጸው ነበር።
ይህ ከትውልድ ትውልድ ይሸጋገራል የተባለው መንገድና ድልድይ፣ በሃገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የመንገድ ግንባታ 10 ዓመታትን ሳይደፍን ከሸዋ ወደ ጎጃምና ጎንደር ለሚጓዙ መንገደኞች ከፍተኛ አደጋን ደቅኗል። ይህንኑ አደጋ ለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ነግረዋቸዋል።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ “ መንገዱን የገነባው የጃፓን ኮንትራክተር ነው። እኛ ጋር ሲመጣ ግን መንገዱ ጃፓን የሰራው አይመስልም። ወይ አፈሩን አላወቁትም፣ ወይ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ተፈጥሯል ወይ የሆነ ነገር አለ ማለት ነው፤ በእኔ በኩል ማድረግ የምችለው እንደገና መንገዱን በሌላ የውጭ ድርጅት ማስመርመርና ለማሰራት መሞከር ነው ሲሉ” መልስ ሰጥተዋል ።
አቶ ሃይለማርያም በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ዙሪያ ምርመራ ለማድረግ ለምን እንዳልፈቀዱ የታወቀ ነገር የለም። ጉዳዩን በቅርብ የተከታተሉ ወገኖች ግን በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ዘመን የተሰራው መንገድ ከፍተኛ ሙስና የተፈጸመበት በመሆኑ፣ ያንን ጉዳይ ላለማንሳት በደፈናው መመለስን ስለመረጡ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ይህ ለ50 ዓመታት ያገለግላል ተብሎ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የወጣበት መንገድ ገና አራት አስርት አመታት እየቀሩት መበላሸቱ፣ አገሪቱ በይስሙላ ግንባታዎች ከፍተኛ ወጪ እያወጣችና ለእዳ እየተዳረገች መሆኑን ማሳያ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎጃም ነዋሪዎች የባቡር ሃዲድ ግንባታው ጎጃምን ሳይነካ ዳር ለዳር ማለፉ ተገቢ አይደለም በማለት ለአቶ ሃይለማርያም ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ አቶ ሃይለማርያምም “ ‹‹አንድ ኪሎ ሜትር ባቡር ለመገንባት 120 ሚልየን ብር እናወጣለን፣ ሁሉም የባቡር መስመሮች በእኛ አቅም የሚገነባ አይደለም። አሁን ብድር ጠይቀን እንኳን ቶሎ ማግኘት አልቻልም፤ በእኛ ፍላጎት ሳይሆን በአበዳሪዎች ፍላጎት የሚወሰን ነው ብለዋል።