በደቡብ አፍሪካ ዳግም የውጭ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች አገረሹ ኢትዮጵያንም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል።

የካቲት ፲፯ ( አሥራ ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ደርባንን ጨምሮ በፕሪቶሪያ በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች በውጭ አገር ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ዳግም
አገርሽተዋል።
ፀረ ስደተኛ አቋም ያላቸው ደቡብ አፍሪካዊያን የተለያዩ የእጅ መሳሪዎችን በመያዝ በስደተኞች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በበኩላቸው ድርጊቱን ”ፀያፍ” ሲሉ ኮንነውታል።
አንድ የውጭ አገር ስደተኛ ”ለምን ትጠሉናላችሁ?” ”ስለምን ትጠሉናላችሁ?” እያለ የተናገረው የቪዲዮ ምስል በአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ተሰራጭቷል። የአገሪቱ ፖሊስ በበኩሉ ነውጠኞቹን ከስደተኞች መኖሪያ አካባቢዎች እንዲርቁ በማድረግ ተቀጣጣይ አስለቃሽ ጋዝ እና ውሃ በመጠቀም አመጹ ጋብ እንዲል ያደረገ ሲሆን ከአድማው ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የተወሰኑ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሏል። በደቡብ አፍሪካ ፀረ ስደተኛ ተቃውሞዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ የቀጠሉ ሲሆን እ.ኤ.አ. 2015 በደርባን ከተማ ውስጥ ብቻ ስድስት ስደተኞች ሲገደሉ፣ በተመሳሳይም እ.ኤ.አ. 2008 ስድሳ ንጹሃን ስደተኞች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ሜይል ኦን ላይን ዘግቧል።