ኢሳት (የካቲት 16 ፥ 2009)
በቀጣዩ አመት በኢትዮጵያ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ መንግስት 180ሺ ዲጂታል ታብሌቶች (ዘመናዊ የእጅ ኮሚውተሮችን) ግዢ እንዲፈጸም ወሰነ።
ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ በአብዛኛው በገጠር የሃገሪቱ አካባቢዎች ለሚካሄደው ለዚሁ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የእጅ ኮምፒውተሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ሃላፊዎች ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ዘማናዊ ያእጅ ኮምፒውተሮቹን ግዢ ለመፈጸም መንግስት በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የሚመድብ ሲሆን፣ በትንሹ የአንዱ ኮምፒውተር ዋጋ እስከ 200 ዶላር አካባቢ እንደሚገመት ለመረዳት ተችሏል።
ባለፈው አመት የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ለህዝብና ቤቶች ቆጠራው ከ30 ሚልዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልግና ለዚሁ ወጪ አለም አቀፍ ድጋፍ እንደሚጠበቅ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
መንግስት የ180ሺዎቹ ዘመናዊ ዲጂታል ግዢ በሂደት ላይ መሆኑን ቢገልጽም ግብይቱ ከየትኛውም ሃገር ወይም ኩባንያ እንደተፈጸመ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
ለዚሁ የሰዎችንና የቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን ባለፈው አንድ አመት የተቋቋመ ሲሆን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለዚሁ ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ ሆነው ባለፈው አመት የተሾሙ ሲሆን፣ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱና ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት የኮሚሽኑ አባላት መሆናቸው ተመልክቷል።
የመጨረሻው የሰዎችንና ቤቶች ቆጠራ በ1999 አም በተካሄደበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 76 ሚሊዮን መድረሱ ይፋ ተደርጎ እንደነበር የሚታወስ ነው።
የአለም ባንክ የሃገሪቱ የህዝብ ቁጥር እንደፈረጆቹ አቆጣጠር በ2016 አም 99.3 ሚሊዮን መድረሱን በድረ-ገጹ ካሰፈረው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
በቀጣዩ አመት በመላ ሃገሪቱ ለሚካሄደው ለዚሁ የሰዎችና ቤቶች ቆጠራ 150ሺ ሰዎች ይመደባሉ ቢባልም ይገዛል የተባለው የኮምፒውተር ቆጠራ ከሚያስፈልጋቸው የሰው ሃይል ቁጥር በላይ መሆኑን መንግስት ይፋ ካደረጋቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁንና የመንግስት ባለስልጣናት ግዢ የመንግስት ባለስልጣናት ግዢ እንዲፈጸም የተወሰነው ዘመናዊ ኮምፒውተር ለምን ከሚያስፈልገው የቆጠራ ባለሙያ ቁጥር በ30ሺ አካባቢ ሊበልጥ እንደቻለ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።