የካቲት ፲፭ ( አሥራ አምስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ የክልሎችን የተሃድሶ ሪፖርት በሰማበት ስብሰባ ላይ የደቡብ ክልል መስተዳድር ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ ከ18 ሺ 250 የበታች አመራሮችን እንዲሁም 1920 ከፍተኛ፣ መካከለኛና ጀማሪ አመራሮች መባረራቸውን ተናግረዋል። በእነዚህ ሰዎች ቦታ ላይ 2 ሺ 359 አዳዲስ አመራሮች መተካታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ደሴ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ አመራሮችን አባረናል ቢሉም ፣ ያባረሯቸውና የተኳቸው ሰዎች ቁጥር ፈፅሞ የማይጣጣም መሆኑና የትኞቹ አመራሮች እንደወረዱ እንዲያስረዱ ቢጠየቁም መልስ መስጠት ባለመቻላቸው ተሰብሳቢዎች ከማጉረምረማቸውም በላይ፣ አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት፣ “የደቡብ ክልል ከ18 ሽህ በላይ አመራሮች እንዳለው አናውቅም ነበር” በማለት አፊዘውባቸዋል።
አቶ ደሴ በገጠር 2099 ሄክታር መሬት እንዲሁም በከተማ 405 ሺ 347 ካሬ ሜትር የተወረሩ ቦታዎችን እና ከ15 ሚልየን ብር በላይ በተለያየ መልኩ የተመዘበረ ገንዘብ ማስመለሳቸውን እንዲሁም 301 ህገ ወጥ ቅጥር እና የደረጃ እድገት ማሰረዛቸውን ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል በተለያዩ መልኩ ያበደረውን 3.9 ቢልየን ብር ገንዘብ መሰብሰብ ባለመቻሉ ደሞዝ ለመክፈልም ሆነ ግንባታዎችን ለማስፈጸም እንዳልቻለ የገለጹት አቶ ደሴ፣ የገንዘብ ችግር በመኖሩ እንደድሮው ከመንግስት ተበድሮ መክፈል እንደማይቻል ፣ ተናግረዋል።
ሌላው በዚሁ አስገራሚ እና እርስ በእርሱ እየተጋጨ በቀረበው ሪፖርት ክልሉ ከ90 ሚልዮን ኩንታል በላይ ምርት አግኝቷል ቢሉም፣ ከ1 ሚሊዮን 200 ሺ በላይ የክልሉ ዜጎች በእለት ደራሽ እህል እርዳታ ስር መሆናቸውንና እርዳታውም እስከ መጪው ታህስሳ ወር እንደሚቀጥል መናገራቸው ነው ፡፡
የአማራ እና የኦሮምያ ክልሎችም ተሃድሶውን በጥራት መምራት ባለመቻላቸው ለስርዓቱ አደጋ እየፈጠሩ ነው በሚል ከህወሃት ትችት ቀርቦባቸዋል፡፡
በኦሮምያ ክልል እስከ ቀበሌ ባሉ ቦታዎች ከ18 ሺ በላይ ባለስልጣናት እንደተባረሩ መዘገቡ ይታወሳል።