የብአዴን መሪዎች የጎንደርን ህዝብ በማባበል ስራ ላይ ቢጠመዱም አልተሳካለቸውም

የካቲት ፲፭ ( አሥራ አምስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ህዝባዊ አመፁ ከተቀሰቀሰ እና አስቸኳይ አዋጅ ከታወጀ በኃላ ባሉት አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ፣ የመከላከያ ሹማምንት ፣ የክልል ፕሬዝዳንቶች ፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶችና ሌሎችም የኢህአዴግ አመራሮች በጎንደር እየተገኙ እራሳቸውን እየሰደቡ፣ ችግሮችን ለመፍታት ሲምሉ እና ሲገዘቱ ቆይተዋል። ለምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን አራተኛ መድረክ፣ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው አምስተኛ መድረክ ፣ ለሁለቱ ምክትል የክልሉ ፕሬዝዳንቶች አቶ ብናልፍ አንዷለም እና ለአቶ አለምነው መኮንን ሶስተኛ መድረክ ሆኖ የተመዘገበ ፣ በጎንደር ከተማ ከተመረጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ፣ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጃችን ውጤታማ ነበር ገምግሙልን” ማለታቸውን ኢሳት ዘግቦ ነበር።
እሁድ እለት ለዘጠነኛ ጊዜ የተጠራው ውይይት በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ሲሆን፣ መድረኩ “ጥልቅ ተሃድሶው በትክክል እየተካሄደ አይደለም፣ ኢህአዴግን ለበለጠ ኪሳራ ዳርጎታል፡፡ እና የክልሉ ህዝብ አንቆ የያዘው አስቸኳይ አዋጁ እንጅ አዋጁ ቢነሳ ከባድ የማይመለስ ችግር ይፈጠራል” የሚለውን የኮማንድ ፖስቱን ሪፖርት ተከትሎ የተዘጋጀ ነው
በስብሰባው ላይ የተገኙትም አንዳንድ የተመረጡ የከተማዋ ነዋሪዎችና የኢህአዴግ ደጋፊ አባላት ናቸው ፣ በስብሰባው ላይ ተሳታፊዎች የተናገሩትም ለኢህአዴግ ባለስልጣናት ጆሮ የሚጥም አልነበረም።
ስብሰባው የውጭ ሃይሎችን እና ኢሳትን በመርገም የተጀመረ ሲሆን፣ “ ስለማራችሁን እናመሰግናለን” በሚል ባለስልጣናቱ ለተሰብሳቢው ምስጋና አቅርበዋል።
አንድ ተሰብሳቢ አስተያየታቸውን ሲሰጡ “ ተሃድሶው ከላይ ወደታች መሄድ አለበት፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ተነስቶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማዛወሩ፣ ድሪቶ በድሪቶ ተለወጠ ከማለት ውጭ” ሌላ ሊባል አይችልም በማለት የኢህአዴግን ባለስልጣናት በድሪቶ መስለዋቸዋል።
“ ህዝቡ በግብር ምክንያት ተማሯል፡፡ ኑሮው አስመርሮታል፣ ግብር አስመርሮታል ፣ በአማራ ክልል መኖር ከባድ ነው” በማለት የተናገሩት ደግሞ አንድ ሴት አስተያየት ሰጪ ናቸው
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ “ ህዝቡን መንግስት እየመራው አይደለም፣ መንግስት ሽባ ሆኗል” የሚል አቋም አለ፣ መንግስትና ህዝብ አልተገናኙም፣ አልተግባቡም፣ ያልተግባባ መንግስትና ህዝብ የልማትና የዲሞክራሲ ስራዎችን ይሰራል ተብሎ አይታሰብም ”ብለዋል
አቶ ደመቀና አቶ ገዱ በተነሱት አስተያየቶች ላይ መልስ ቢሰጡም፣ ተሰብሳቢው ግን ፣ “ አሁን የምትናገሩት ምንም ቋት አይገባም፣ መንግስትም ዝም ብሎ ችግሮችን ከመስማት ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ቢሞክር ይሻለዋል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።