ኢሳት (የካቲት 15 ፥ 2009)
የደቡብ አፍሪካ መንግስት ከአለም አቀፍ የጦር ወንጀሎች ፍርድ ቤት አባልነት ለመውጣት ያስተላለፈውን ውሳኔ የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ረቡዕ ውድቅ አደረገው።
የደቡብ አፍሪካ መንግስት መቀመጫውን ዘ-ሄግ ዘ-ኔዘርላንድስ ያደረገው ፍርድ ቤቱ ፍትሃዊ የሆነ አካሄድ በአህጉሪቷ ላይ አይከተልም በማለት ከፍርድ ቤቱ አባልነት ለመሰናበት ከወራት በፊት ውሳኔን አስተላልፎ እንደነበር ይታወሳል።
ይሁንና የሃገሪቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግስት የወሰደው ዕርምጃ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የተደረገ ነው በማለት ጉዳዩን ወደ ህግ ወስደው እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል።
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤትም የደቡብ አፍሪካ መንግስት ለአመታት በአባልነት ከቆየበት የአለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት ለመሰናበት የወሰነው ዕርምጃ ህገ-መንግስታዊ ድጋፍ የሌለውና ተገቢ አለመሆኑን በውሳኔው አሰምቷል።
የደቡብ አፍሪካ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስት ጉዳዩን ለፓርላማ ሲያቀርብ ውሳኔ መድረሱ ህገወጥ ነው በማለት በአቤቱታቸው አቅርበው የነበረ ሲሆን፣. ፍርድ ቤቱም ይህንኑ ሃሳብ በመደገፍ ሃገሪቱ ከፍርድ ቤቱ አባልነት እንድትወጣ ብይንን ሰጥቷል።
ባለፈው ወር በአዲስ አበባ ከተማ አመታዊ ጉባዔያቸውን አካሄደው የነበሩ የአፍሪካ መሪዎች 34 አካባቢ የሚሆኑ የአህጉሪቱ አባል ሃገራት ከፍርድ ቤቱ እንዲሰናበቱ ውሳኔ አስተላልፈው እንደነበር የሚታወስ ነው።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው የአፍሪካ መሪዎች ከፍርድ ቤቱ በጅምላ ለመሰናበት የያዙት እቅድ በስልጣን ዘመናቸው ለፈጸሟቸው ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ተጠያቂ ላለመሆን ሲሉ ዕርምጃውን ሲቃወሞ ቆይተዋል።
የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን ተከትሎ የሃገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር የሆኑት ማይከል ማሱታ መንግስት በውሳኔው ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ አማራጮችን እንደሚያይ ለሮይተርስ ገልጿል።
የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ ለፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ መንግስት ፈታኝ እንደሚሆን የተነገረ ሲሆን፣ ብይኑ ተመሳሳይ ዕርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት ላላቸው የአፍሪካ ሃገራት መልዕክት ያስተላለፉ እንደሆነም የፖለቲካ ተንታኞች በመግለጽ ላይ ናቸው።
ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ በፍርድ ቤቱ አባል ሃገራት የሆኑት ብቡሩንዲ እና ናሚቢያ ከአባልነት ለመውጣት እቅድ እንዳላቸው በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ዘጋምቢያ በበኩሏ በቀድሞው ፕሬዚደንቷ በኩል ከአባልነት ለመውጣት ውሳኔን ብታስተላልፍም በምርጫ ሽንፈት የተሰናበቱት የቀድሞ ፕሬዚደንት ያህ’ያ ጃም’ህ ያስተላለፉት ውሳኔ በአዲስ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት አዳማ ባሮ እንዲሻር ተደርጓል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የአፍርካ አባል ሃገራት ከፍርድ ቤቱ እንዲሰናበቱ የማግባባት ዘመቻን ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወቃል።