ኢሳት (የካቲት 14 ፥ 2009)
ሩሲያ በቀጣዮቹ ሶስት አመታት ለግብፅ 50 ተዋጊ አውሮፕላኖችን ለማቅረብ ከሃገሪቱ ጋር ስምምነት መድረሷን የሩሲያ ወታደራዊ ባለስልጣናት ማክሰኞ ይፋ አደረጉ።
የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የግብፁ አቻቸው አብደል ፈታህ አልሲሲ በቅርቡ ባደረጉት ውይይት ተዋጊ ጀቶች እንዲቀርቡ ስምምነት ተደርሶ እንደነበር አህራም የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ይሁንና የግብጽ ባለስልጣናት ከሩሲያ ጋር ተደርሷል የተባለውን ስምምነት መቼ እንደተደረሰና በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ የተዋጊ ጀቶቹ አቅርቦት በሩሲያ ታሪክ ግዙፍ እንደሆነ ተነግሯል።
በተባበሩት አረብ ኤሜሬት እየተካሄደ ባለ ወታደራዊ ኤግዚቪዥን ላይ የተገኙት የሩሲያ የወታደራዊ ትብብር አገልግሎት ምክትል ሃላፊ የሆኑት አሌክስ ፍሮልኪን ሃገራቸው እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2020 ሚግ-29 የተሰኙ 50 ተዋጊ ዘመናዊ ጀቶችን ለማቅረብ ጥረት እያደረገች መሆኑን ለመገኛኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ዘመናዊ የተባለው ሚግ-29 የጦር ጀት ሁለት R-27 የተባሉ ሚሳይሎችን የመሸከም አቅም ያለው ሲሆን፣ 3ሺ ኪሎግራም የሚመዝን ቦምብ በአንድ ጊዜ እንደሚያጓጉዝ ታውቋል።
ከአሜሪካ ተመሳሳይ የጦር መሳሪያ አቅርቦት የምታገኘው ግብፅ በተለይ እንደፈረጆቹ አቆጣጠር ከ 2017 ጀምሮ የጦር መሰረተ-ልማቷን በዘመናዊ መልኩ ለማደራጀት ወስና እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ አህራም ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል። ሃገሪቱ እነዚህን ዘመናዊ የጦር ተዋጊ ጀቶች ለመረከብ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ስምምነት መፈጸሟንም የሩሲያ ወታደራዊ ሃላፊዎች ገልጸዋል።
ግብፅ 50 የሚሆኑትን ሚግ-29 ተዋጊ ጀቶች በተያዘላቸው የጊዜ ቀጠሮ ለመረከብ ሩሲያ ጋር ድርድት እያደረች እንደሆነም ተመልክቷል።
ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖቹ የአየርና የምድር ኢላማዎችን በቀላሉ ለማውረድም አቅም ያላቸው ሲሆን፣ የጦር ጀቶቹ ከአሜሪካው F-15 እና F-18 ዘመናዊ ጀቶች ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው ከወታደራዊ መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል። የጦር ጀቱ ከሚሸከማቸው ሚሳይሎች በተጨማሪ 60 እና 30 የተሰኙ አውቶማቲክ መድፎችን የሚይዝ እንደሆነም ታውቋል።
በቅርቡ ከግብፅ ፕሬዚደንት ጋር የስልክ ልውውጥ ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሃገራቸው ግብፅ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2015 አሜሪካ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የሚገመት የጦር መሳሪያን ለግብፅ አቅርባ እንደነበር ታውቋል።