ኢሳት (የካቲት 13 ፥ 2009)
በደቡብ ሱዳን ሁለት ግዛቶች ረሃብ መከሰቱን እና የ100ሺ ሰዎች ህይወት አደጋ ውስጥ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰኞ ይፋ አደረገ።
በደቡብ ሱዳን ለሶስት ተከታታይ አመታት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት እንዲሁም በቅርቡ በሃገሪቱ የተከሰተው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለረሃብ መከሰት አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን ድርጅቱ አስታውቋል። አቅም ያገኙ ደቡብ ሱዳናውያን ረሃቡን በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ በመሰደድ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ በከፍተኛ የድርቅ አደጋ ውስጥ ሲሆኑ፣ በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ሁለት ግዛቶች የድርቅ አደጋው ወደረሃብ ሲሸጋገርባቸው የመጀመሪያዎቹ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
በሃገሪቱ ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎች አካባቢ በከፋ የምግብ እትጥረት ውስጥ በመሆናቸው በሁለት ግዛቶች የተከሰተው ይኸው ረሃብ ወደሌሎች አካባቢዎች ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም የድርጅቱ ሃላፊዎች ለመገኛኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
“ስንሰጋ የነበረው ጉዳይ እሙን ሆኗል” ያሉት የደቡብ ሱዳን የአለም ምግብ ፕሮግራም ተወካይ ስርጅ ቲሶት፣ የረሃቡ አደጋ የበርካታ ደቡብ ሱዳናውያን ህይወትን ሊቀጥፍ እንደሚችል ተናግረዋል።
በሃገሪቱ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት ተወካይ የሆኑት ጀርሚ ሆፕኪንስ በበኩላቸው በረሃቡ አደጋ ከ250ሺ የሚበልጡ ህጻናት ሊሞቱ እንደሚችሉ ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት ረሃቡ በሁለት ግዛቶች መከሰቱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ 5.5 ሚሊዮን ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው እንደሚገኙ ገልጿል።
በተባበሩት መንግስታት የቀረበው ይኸው የረሃብ ሪፖርት የፕሬዚደንት ሳልቫኪር መንግስት ለተረጂዎች ወቅታዊ እርዳታ እንዳይደርስ አስተጓጉለዋል ሲል ቅሬታ ማቅረቡንም ቪኦኤ እንግሊዝኛው ክፍል ዘግቧል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1998 አም ደቡብ ሱዳን ከጎረቤት ሱዳን ነጻነቷን ለማካሄድ ስታካሄድ በነበረው ጦርነት ተመሳሳይ የረሃብ አደጋ አጋጥሞ ወደ 700ሺ የሚጠጉ ሰዎች ሞተው እንደነበርም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁንና ሰው ሰራሽ ነው የተባለው እና በዩኒቲ ግዛት የተከሰተው አዲሱ የረሃብ አደጋ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት የከፋ ሊሆን እንደሚችል ተተንብዮአል።
በማዕከላዊ ኢኳቶሪያል የደቡብ ሱዳን ግዛት ተመሳሳይ የረሃብ አደጋ ግማሽ ሚሊዮን በሚሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን፣ አለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማት በህይወት ማዳን ስራ ላይ እንደሚሰማሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳስቧል።
በሃገሪቱ ተባብሶ የቀጠለው የእርስ በርስ ግጭትም ወደ ዘር ግጭት እያመራ ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ ስጋቱን መግለጹ ይታወሳል።