የካቲት ፲፫ ( አሥራ ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መገኛ ምንጫቸው በትክክል የማይታወቁና በኮንትሮባንድ ጭምር እንደሚገቡ የሚነገርላቸው የተለያዩ መድሃኒቶች በአዲስአበባ በሚገኙ በአንዳንድ ሕጋዊ መድሃኒት መሸጫ ፋርማሲዎች፣ ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች እየተቸበቸቡ ነው፡፡
መድሃኒቶቹ በተለያዩ መጠቅለያዎች ተጀቡነው ድንበር አቋርጠው የሚገቡ መሆናቸውን፣ ከመንግሥት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በአንዳንድ ምግባረ ብልሹ ሠራተኞች እየተመዘበሩ በፌስታልና በመሳሰሉ ጥንቃቄ በጎደላቸው መያዣዎች ወደፋርማሲዎቹ እንደሚሸጋገሩ ፍንጭ መኖሩን ከጤና ቢሮው የተገኘ መረጃ አመልክቷል፡፡
በእንዲህ ዓይነት መልኩ እየተሰራጩ ያሉ መድሃኒቶች የሕሙማንን ችግር በማባባስ እስከሞት የሚደርስ አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ሙከራዎች ቢኖሩም አጥጋቢ ከአለመሆናቸው ጋር በተያያዘ ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ ምንጫችን ጠቅሶአል፡፡
በኮንትሮባንድ ከሚደረገው የመድሃኒት ስርጭት በተጨማሪ በመንግስት በሕጋዊ መንገድ ይገዛሉ የተባሉ መድሃኒቶችም ቢሆኑ ከጥራት አኳያ ከፍተኛ ችግር አለባቸው ተብሎአል፡፡ ከግዥ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ በሚፈጸም ሙስናና ብልሹ አሰራር ደረጃቸውን ያልጠበቁ መድሃኒቶች ተገዝተው የሚሰራጩበት ሁኔታ መኖሩ፣ ከተገዙም በሁዋላ በተለያየ ምክንያት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ጭምር በቸልተኝነት የመሸጥ ሁኔታ መኖሩ፣ መድሃኒቶቹን ከማጓጓዝና ማከማቸት አንጻር ተገቢው ጥንቃቄ ባለመደረጉ ለብልሽት የሚዳረጉበት ሁኔታ መኖሩ የህብረተሰቡ ጤና ይበልጥ እንዲቃወስ መንስኤ እየሆነ ነው ተብሎአል፡፡
በያዝነው ዓመት ብቻ ከዘጠኝ በላይ ፋርማሲዎች ላይ በተደረገ ክትትል ከተፈቀደላቸው ውጪ ሲሰሩ በመገኘት፣ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ምንነታቸው የማይታወቁ መድሃኒቶችን በማሰራጨት ሥራ ውስጥ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቆአል፡፡