የካቲት ፲፫ ( አሥራ ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመጽ ምክንያት የተለያዩ አገራት ማንኛውንም ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የጉዞ እቀባ መጣላቸውን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቁጥራቸው ከ100 ሺህ በላይ አገር ጎብኚ ቱሪስቶች መቅረታቸውን የጁሚያ ትራቭል ጥናትን በመጥቀስ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
ከሁለት ዓመት በፊት 900 ሺህ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. 2016 ወደ ኢትዮጵያ የመጡ አገር ጎብኚዎች 800 ሺህ ናቸው። ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ቱሪስቶች ለጉዟቸው መቋረጥ በምክንያትነት ያስቀመጡት የአገሪቷ ሰላም ማጣት እና በአስቸኳይ የጊዜ አዋጅ ስር መሆኗን ሲሆን እስካሁንም አብዛሃኛው አገራት የጣሉትን የጉዞ ማእቀብ አላነሱም።
ከጸጥታ እና ደኅንነት ስጋቶች በተጨማሪ በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመሟላት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ፣ የቱሪዝም ሀብቶች እንደሚገባቸው አለመተዋወቃቸው፣ የአገር ውስጥ ጐብኚዎች የጉብኝት ልማድ ዝቅተኛ መሆን ለቱሪዝም ገቢው ማሽቆልቆል በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መዝገብ ውስጥ ከአሥር በላይ የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከቱሪዝም ዘርፍ ማግኘትና መጠቀም የሚገባትን ያህል ሳትጠቀም ቀርታለች።