የካቲት ፲ ( አሥር )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 997 ሺ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተለያዩ የቤት ግንባታ መርሃግብሮች በመመዝገብ ከምግብና ከሌሎች ፍጆታቸው በመቀነስ በየወሩ እየቆጠቡ ባንክ ያስገባሉ። አብዛኛው ህዝብ 20 በ 80 በሚባለው መርሃ ግብር ተመዝግቦ ቤቶችን በመጠባባቅ ላይ ቢሆንም፣ መስተዳዳሩ ባጋጠመው ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት የተነሳ የተጀመሩ ግንባታዎችን 80 በመቶ ለማድረስ የነበረውን እቅድ ሳይሳካ የቀረ ሲሆን፣ በአብዛኛው የግንባታ ቦታዎችም ስራዎች ቆመዋል። በዚህ አመት አዲስ ይጀመራል የተባሉ አዳዲስ ግንባታዎችም እንደማይጀመሩ ታውቋል። አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ግን በያዝነው ዓመት መጨረሻ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለሕዝቡ እንደሚተላለፉ በቅርቡ በፓርላማ መድረክ ላይ ተናግረው ነበር። የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ግን ዘንድሮ ቤቶቹን ለማስተላለፍ ዝግጁ አለመሆኑን ዘጋቢያችን መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
40 በ60 የቤቶች ፕሮግራም ደግሞ ከ160 ሺ በላይ ሕዝብ ተመዝግቦ እየተጠባበቀ ያለ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት ይተላለፋሉ የተባሉት 1,292 ቤቶች እስከ ዛሬ ሳይተላለፉ ቀርተው አሁን ደግሞ በቀጣይ ሁለት ወራት ለባለዕድለኞች ይተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃው ያመልክታል፤፡
እነዚህ ይተላለፋሉ የተባሉ የ40 በ60 ቤቶች ከተመዘገበው ሕዝብ ቁጥር አንጻር ሲመዘኑ ቁጥራቸው እጅግ አናሳ መሆኑ ቆጣቢዎችን ተስፋ አስቆርጦአል፡፡