የካቲት ፱ ( ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ሸዋ ዞን በሚዳ ወረሞ ከተማ ወጣቶች ትናንት ምሽት የቅስቀሳ ወረቀቶችን የበተኑ ሲሆን፣ ዛሬ ጠዋት ከያቅጣጫው ሲሰባሰቡ ከመርሃቤቴ የተነሱ ፖሊሶች እንደበታተኑ በማድረግ ከተማዋን ተቆጣጥረዋል።
ወጣቶቹ በመሰባሰብ ላይ እያሉ ፖሊሶች ነጣጥለው በማጥቃት እንዲበተኑ ያደረጉ ሲሆን፣ባለፈው ሳምንት ታስሮ በድጋሜ ተለቆ የነበረው የቀድሞው የደህንነት ሰራተኛ ወጣት አብዩ ሰይድ በድጋሜ ታፍኖ ተወስዷል። ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በፖሊሶች የተወረረች ሲሆን፣ ትናንት ምሽት ላይ ፖሊሶች፣ “በሰልፉ ላይ በሚወጡት ወጣቶች ላይ ለሚወሰደው እርምጃ መንግስት ተጠያቄ አይሆንም” በማለት በድምጽ ማጉያ ሲለፍፉ አምሽተዋል።
ሙዚቃ ቤቶችና ቡና ቤቶች በፖሊሶች ድርጊት በመቆጣት “ ሰከን በል” የሚለውን የአርቲስት ይሁኔ በላይ ሙዚቃን በድምጽ ማጉያ በመልቀቅ መልዕክት ሲያስተላልፉ ውለዋል።
ባለፈው ሳምንት ወጣቶች ወረቀቶች ከበተኑ በሁዋላ፣ የጸጥታ ሃይሎች በአካባቢው እንዲሰፍሩ መደረጉን የአይን እማኞች ተናግረዋል።