በቡሌ ሆራ ከተማ በርካታ ወጣቶች በእስር ቤት ስቃይ እየደረሰባቸው ነው

የካቲት ፱ ( ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት በምዕራብ ጉጂ ዞን በቡሌ ሆራ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በተለያዩ ክፍሎች፣ በእያንዳንዱ 3 በ 4 ሜትር በሆነ አነስተኛ ክፍል ውስጥ እስከ 50 ሰዎች ታጉረው ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው ነው። በአካባቢው ከነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የታሰሩት በመቶዎች የሚቆጠሩት ወጣቶች፣ በምግብ እጥረት እየተሳቃዩ ነው። ፖሊስ ጣቢያ በሚታሰሩበት ወቅት ምግብ የማይቀርብላቸው በመሆኑና ቤተሰቦቻቸውም እንደ ልባቸው ምግብ ማስገባት ባለመቻላቸው ፣ እስረኞች ለወራት በስቃይ ላይ እንደሚገኙ የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ። “ወይ ወደ ጦላይ ተልከው እንደ ሌሎቹ ምግብ እየተመገቡ አልታሰሩ፣ ወይም ጉዳያቸው ታይቶ እንዲፈቱ አልተደረገ፣ ሰዎቹ በስቃይ እንዲሞቱ እየተደረገ ነው “ ሲሉ የእስረኞች ቤተሰቦች ምሬታቸውን ተናግረዋል።
የእስሩ ዘመቻ አሁንም ድረስ የቀጠለ ሲሆን፣ በገላና ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ በድሉ መንግስቱ አፈሳውን በመፍራት ወደ ሌላ ቦታ ቢሄዱም፣ ወታደሮች የእርሳቸውን ባለቤት በማሰርና ወደ ጦላይ በመላክ ለሳምንታት እንዲታሰሩ አድርገዋል። አቶ በድሉ ባለቤታቸውን ለማስፈታት ለኮማንድ ፖስት ደብዳቤ ሲጽፉ፣ እርሳቸውንም ይዘው ማሰራቸውንና በአሁኑ ሰአት በእስር ቤት ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በነገሌ ቦረና ዞን በሊበን ወረዳ የሶማሊ ልዩ ሃይል በቦረና ኦሮሞዎች ላይ የሚያካሂዱትን ጥቃት መቀጠላቸውንና በርካታ ሰዎች መገደላቸውም የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ። በግጭቱ እስካሁን የሞተውን ሰው በትክክል ለማወቅ ባይቻልም አንዳንድ ሰዎች እስከ 60 ይደርሳል ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል።
ግጭቱ እስከትናንት መቀጠሉና በአካባቢው ዛሬም ድረስ ከፍተኛ ውጥረት መኖሩን ምንጮች ይገልጻሉ።