የካቲት ፱ ( ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የታሪክ፣ ባህል እና የምጣኔ ሃብት ባለሞያ ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 3 ቀን1927 እንግሊዝ ውድፎርድ ግሪን ከተማ ውስጥ ተወለዱ። ለንደን በሚገኘው ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የኢኮኖሚካዊ ታሪክ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት እናታቸውን ወ/ሮ ሲልቪያ ፓንክኸርስት ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ መምህር በመሆን አገልግለዋል። በደርግ መንግስት ወቅት ኢትዮጵያን ጥለው የተሰደዱት ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በጥናትና ምርምሮች በስኮላርሽፕ ትምህርት መስክ በተለያዩ ዘርፎች በመሳተፍ ኢትዮጵያን ማገልገላቸው ይታወሳል።
የጸረ ፋሽሽት የነጻነት አርበኛዋን የእናታቸውን ወ/ሮ ሲልቪያ ፓንክኸርስትን ፈለግ ተከትለው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ሁሉ አበርክተዋል። ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በዘጠናኛ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።