የኢትዮጵያና የሱዳን መንግስት ተወካዮች የድንበር ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር በመቀሌ ተሰባሰቡ

ኢሳት (የካቲት 8 ፥ 2009)

የኢትዮጵያና የሱዳን መንግስት ተወካዮች በሁለቱ ሃገራት መካከል ስላሉ የድንበር ይገባኛል ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ሃሙስ በመቀሌ ከተማ ምክክር እንደሚጀምሩ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ በኩል ከአማራ፣ ቤኒሻንጉልና, የትግራይ ክልሎች የተወከሉ ባለስልጣናት ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን፣ ከሱዳን በኩል ደግሞ የጋዳሬፍ፣ የብሉናይል፣ የሴርናና፣ የከሰላ ግዛት ተወካዮች ለሁለት ቀን በሚቆየው ምክክር ተሳታፊ እንደሚሆኑ ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።

የኢትዮጵያና የጎረቤት ሱዳን ተወካዮች በሚሳተፉበት በዚሁ መድረክ በሁለቱ ሃገራት መካከል ከድንበር ይገባኛል ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች ምክክር የሚካሄድባቸው ሲሆን፣ የሱዳን ተወካዮች በኢትዮጵያ ተወስዶብናል የሚሉትን የእርሻ መሬት እንደሚጠይቁ ሃላፊዎች ለጋዜጣው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ከሁለት አመት በፊት ድንበሮቻቸውን ለማካለል ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

ይሁንና የሁለቱ ሃገራት በፕሬዚደንት ደረጃ የተፈራረሙትን ስምምነት ተከትሎ በተለያዩ አለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስምምነቱ የኢትዮጵያን መሬት አሳፍሎ የሚሰጥ እርምጃ ነው በማለት ተቃውሞ ሲያካሄዱ ቆየተዋል።

የኢትዮጵያ የድንበር ኮሚቴ እንዲሁ ኢትዮጵያ እና ጎረቤት ሱዳን ድንበራቸውን ለማካለል የደረሱት ስምምነት በፓርላማ ደረጃ እንኳን ምክክር ያልተካሄደበትና ድርጊቱ የሃገሪቱን ጥቅም የሚጎዳ እንደሆነ በተደጋጋሚ ቅሬታን አቅርቧል።

በመቀሌ በሚጀመረው ምክክር ላይ የሚሳተፉት የሱዳኑ የጋዳሬፍ ግዛት ገዢ የሆኑት ሚርጋኒ ሳሊህ ሲድ አህመድ በጉባዔው በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በኩል ተወስዶብናል ያሉት መሬት እንዲመለስላቸው ጥያቄን እንደሚያቀርቡ ለሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ይፋ አድርገዋል።

ከዚሁ የጋዳሬፍ ግዛት የሚነሱ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ካለፉት ጥቂት አመታት ጀምሮ በድንበር ዙሪያ ያለው ግዛት ለእኛ የተሰጠ ነው በማለት በኢትዮጵያ በኩል ያሉ አርሶ አደሮችን ሲያፈናቅሉ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ሲገልጹ ቆይተዋል።

የግዛቱ ሃላፊ በኢትዮጵያ ተወስዶብናል ያሉትን መሬት ለማስመለስ ጥያቄን እንደሚያቀርቡ ቢያስታውቁም ጥያቄው በኢትዮጵያ በኩል በምን መልኩ እንደሚስተናገድ የታወቀ ነገር የለም።

የግዛቱ ሃላፊ ሲድ አህመድ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2004 አም ኢትዮጵያና ሱዳን የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የሱዳን ግዛት በሚባሉ አካባቢዎች የእርሻ ስራን እንዲያከናዉኑ ስምምነት ተደርሶ እንደነበርና ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ጥያቄ እንደሚያቀርቡም አክለው ገልጸዋል።

ይሁንና ከ10 አመት በፊት ተደርሷል የተባለው ይኸው ስምምነት በምን መልኩ ድንበሩን አካሎ (ለይቶ) እንደነበር የሱዳኑ ተወካይ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።

የሱዳን ባለስልጣናት በከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ ሳይቀር ድንበሩን ለማካለል ስምምነት መደረሱን ቢገልጹም፣ የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።