በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ አስታወቀ::

የካቲት ፯ ( ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሚያካሂደው 34ኛው መደበኛ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈፀሙትን ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶት አትኩሮት በመስጠት እንዲያወግዝ ሲል የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ ጥሪውን አቅርቧል። በኢትዮጵያ የአስቸኳይ የጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ በተለይ በወጣት የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ግድያ፣ እስራት፣ ከአገር ማሳደድ፣ አካላዊ ጥቃቶችን ጨምሮ የተለያዩ ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች ከበፊቱ በከፋ ሁኔታ ተባብሶ መቀጠሉን በሪፖርቱ አስታውቋል።
ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ተከትሎ ገዥው ፓርቲ በሕገ መንግስቱ የተደነገጉ መሰረታዊ የሆኑ መብቶቻቸውን በሰላማዊ መንገዶች የጠየቁ ወጣቶች ላይ የጸጥታ ሃይሎች ከአቅም በላይ የሃይል አማራጮችን እየተጠቀሙ ነው። ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ሕዝባዊውን ጥያቄዎችን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ የጅምላ ጥቃቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ገዥው መንግስት በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተው የነበሩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎችንም የመግደል፣ የማሰር እና የማሳደድ ዘመቻውን ገፍቶበታል። የኦሮሞ ፌደራሊስት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ የፓርቲውን ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ጓደኞቻቸውን አቶ ታዬ ነገራ እና አቶ ኩማላን ጨምሮ አያሌ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት በጅምላ ታስረዋል። በእስር ቤቶች ውስጥ ያሉ እስረኞች በተጨናነቀ ክፍል ውስጥ ታጉረው ሰቆቃ ይፈፀምባቸዋል። በእስር ቤቶች ውስጥ ኦሮሚኛ ቋንቋ ብሄራዊ ቋንቋ እስኪመስል ድረስ በኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ላይ የከፋ ግፍ እየተፈጸመ ነው። እስካሁን ድረስም ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከስራ ገበታቸው የተወሰዱ በርካታ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ያሉባቸው አድራሻዎች አይታወቁም። ለሰላማዊ ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ ሕጋዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ገዥው ፓርቲ በኢሬቻ በዓል ላይ ከ700 በላይ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የጅምላ ፍጅት መፈፀሙን ሪፓርቱ አትቷል።
እስካሁንም በአጠቃላይ በክልሉ ቁጥራቸው ከአንድ ሽህ በላይ የሚሆኑ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች በጭካኔ ተገለዋል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ፣ ከ40 ሽህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ደግሞ ከወላጅ ዘመዶቻቸው እና ከአካባቢያቸው ርቀው በሚገኙ ወታደራዊ ካንፖች ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ የምርመራ ሪፖርቱ አመላክቷል። በምስራቅ እና ምእራብ አርሲ ዞኖች ውስጥ ብቻ 248 ዜጎች በግፍ ተገለው ሕይወታቸው ሲያጡ ፣ ከ3 ሽህ 706 በላይ ደግሞ በጅምላ ታስረዋል። የሟቾች እና ታሳሪዎች ሙሉ ስም እና አድራሻዎች ዝርዝር በመረጃ አስደግፎ የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ መግለጫ አውጥቷል።
በሃረርጌ፣ ባሌ፣ በወለጋ ክፍለሃገሮች በምስራቅ ሸዋ እና ምዕራብ ሸዋ የተገደሉትን እና የታሰሩ ዜጎችን አድራሻም በሪፓርቱ ውስጥ ተካቷል። ቁጥራቸው ከ28 በላይ የሚሆኑ የሕክምና ዶክተሮች፣ ሲቪል ኢንጅኒነሮች፣ የዩንቨርሲቲ መምህራን እና በከፍተኛ የሙያ መስክ ላይ የተሰማሩ ምሁራን በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን የስራ ድርሻቸውን እና ይሰሩበት የነበረውን መስሪያ ቤቶችም ጭምር በሪፖርቱ ውስጥ ተካቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት እንዲያቆም ግፊት እንዲያደርጉ እና በገዥው ፓርቲ የተፈጸሙት ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ ሲል የምስራቅ አፍሪካ የሰብዓዊ መብት ሊግ ጥሪውን አቅርቧል።