የካቲት ፯ ( ሰባት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያ በታችኛው የኦሞ ሸለቆ የገነባችውን ግድብና እያካሄደች ያለውን ልማት ተከትሎ የኬንያ ቱርካና ሀይቅ የውሃ መጠን መቀነሱ በግማሽ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን ህይወት ላይ አደጋ መጋረጡት ዓለማቀፉ የስብ አዊመብት ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዎች አስታውቋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ በዩናይትድ ስቴትስ የእርሻ ዲፓርትመንት ለሕዝብ ክፍት የሆኑ የዳታ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳለው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥር 2015 ጀምሮ የቱርካና ሀይቅ ከፍታ በ1 ነጥብ 5 ሜትር ዝቅ ያለ ሲሆን ወደፊትም ከዚህ በከፋ ሁኔታ ሊቀንስ ይችላል።
በተቋሙ ምርምር ክፍል በሳተላይት የተነሳ ምስልም የሀይቁ ከርስ ላይ ጉዳት መድረሱን እንደሚያሳይ የጠቀሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች ከህዳር 2014 ወዲህ 1 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የሚሆን የፈርጉሰን ሰላጤ አካል ለውድመት መዳረጉን ጠቁሟል።
ይህ የፈርጉሰን ሰላጤ ልዩ የዓሳ መራቢያ ቦታ ሲሆን፤ ለሀገሬው የቱርካና ህዝቦች ቁልፍ የአሳ ማምረቻ ቦታቸው ሆኖ የቆዬ ነው።
ወደ ሀይቁ ከሚገባው ውሃ ይቀንሳል ተብሎ የሚገመተው የውሃ መጠን በኢትዮጵያና በኬንያ በሚገኙትና ግማሽ ሚሊዮን በሚሆኑት የታችኛው ኦሞ ሸለቆና የቱርካና ነዋሪዎች የምግብ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል የሂዩማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ ተማራማሪ ፍሌክስ ሆርነ ገልጸዋል።
ሆርነ አክለውም፦”የኢትዮጵያ መንግስት ለልማት እየወሰደ ያለው እርምጃ በአካባቢው የሚገኙ ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ መጣል የለበትም” ብለዋል።
በቱርካና በአሳ እርባታ የሚተዳደሩ ሰዎች በ2016 ለሂዩማን ራይትስ ዎች በሰጡት አስተያዬት በግልገል ጊቤ ሦስት ግንባታ ምክንያት አደጋ ሊፈጠርባቸው እንደሚችል መስጋታቸውን ሆኖም አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ግንባታው በራሳቸው ህይወት ላይ ሊፈጥር ስለሚችለው ተጽእኖ ያልተገነዘቡ እንደነበሩ ተቋሙ ጠቁሟል። በወቅቱ ሂዩማን ራይትስ ዎች በፈርጉሰን ሰላጤ አካባቢ ባደረገው ጉብኝት አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች የቱርካና ሀይቅ መጠን ከወትሮ እንደቀነሰ መገንዘባቸውን በሪፖርቱ አውስቷል።.
ይህ በመሆኑም ህይወታቸውን በዓሳ እርባታ ላይ መሰረት ያደረጉ ዓሳ አርቢዎች በየ ዕለቱ የሚያጠምዱት አሳ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ይናገራሉ። አንዲት የ50 ዓመት ሴት ለሰባዊ መብት ተቋሙ ሲናገሩ” በአሁኑ ወቅት ነገሮች አስቸጋሪ ሆነውብናል። ትልቁ ችግራችን ረሀብ ሆኗል።ምክንያቱም የሀይቁ ውሃ ቀንሶብናል”ብለዋል።
የኬንያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመነጋገር ግፊት ለማድረግ ካለመሞከሩም በላይ በችግሩ ተጠቂ ከሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመመካከር በኩል ይህን ያህል ያደረገው ነገር አለመኖሩም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያና የኬንያ መንግስታት ከተፋሠሱ ግርጌ የሚሰሩት ግንባታዎች ከታች የሚኖሩትን ሰዎች ህይወት እንዳያጠፉ በማድረግ-የተጠቂዎቹን ዜጎች ደህንነት በማረጋገጥ በኩል አፋጣኝ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ ሂዩማን ራይትስ ዎች አሣስቧል።