ኢሳት (የካቲት 6 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህዝቡን ጥያቄ የመለሰ ባለመሆኑ ህዝባዊ ተቃውሞ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል የብሪታኒያው ዘጋርዲያን ጋዜጣ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረገውን ቃለመጠይቅ ዋቢ በማድረግ ዘገበ።
አዋጁ ተቃውሞን ለመቆጣጠር ተግባራዊ ቢያደርግም ህዝቡ ሲያነሳ የነበረው የተለያየ ጥያቄ እስካሁን ድረስ ምላሽ አለማግኘቱን በኢጄሬ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለደህንነታቸው ስማቸውን እንዳይገለጽ በመጠየቅ ለጋዜጣው ተናግረዋል።
በምዕራብ ሸዋ የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአስቸኳይ የጊዜ አዋጁ ምክንያት ተቃውሞው መረጋጋትን ቢያሳይም የመንግስት ባለስልጣናት የገቡትን ቃል ባለመተግበራቸው ህዝባዊ ተቃውሞ ዳግም ሊያገረሽ እንደሚችል አስታውቀዋል።
በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ህዝባዊ ተቃውሞ የአዲስ አበባ ከተማን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት የተያዘውን ዕቅድ መነሻ አድርጎ ቢቀሰቀስም፣ ህዝቡ የተለያዩ የዴሞክራሲና የፍትህ ጥያቄ እንዳለው ይገልጻሉ።
የፌዴራል እና የክልሉ ባለስልጣናት ከህዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡ በተደጋጋሚ ቃልን ቢገቡም እስካሁን ድረስ ህዝባዊ ጥያቄውን መሰረት ያደረገ ዕርምጃ እንዳልተወሰደ ነዋሪዎቹ ለጋዜጣው አስረድተዋል።
የአስችኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መደረግ በትንሹ 25ሺ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ያወሳው ዘጋርዲያን፣ ቃለ-መጠይቅ ያደረገላቸው ነዋሪዎች ትርጉም ያለው ለውጥ ማየት እንደሚሹ መናገራቸውን በሪፖርቱ አስነብቧል።
በሃገሪቱ ያለው የአንድ የፓርቲ የበላይነት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያላቸውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ እንዲሁም ማህበራዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኝ አስተዋጽዖ ማድረጉንም የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ከጋዜጣው ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
በኦሮሞ ብሄር ዘንድ “ባል ያለውን ሚስት መቀየር አትችልም” የሚል አባባል እንዳለ የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ገዢው የህወሃት (ኢህአዴግ) መንግስት በሃገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት እንዲህ ያለ አገዛዝን ተግባራዊ አድርጎ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ በምዕራብ አቅጣጫ በ130 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የጉዳር ከተማ ነዋሪዎች የአርሶ አደር ይዞታዎችን ያለምንም በቂ ካሳና ምትክ ቦታ ለማስለቀቅ ሲካሄድ የቆየው ዘመቻ ህብረተሰቡ ጥያቄን እንዲያነሳ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
ለአንድ አመት ያህል በክልሉ ቀጥሎም በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ እንደብሪታኒያ ላሉ የምዕራባዊያን መንግስታት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የልማት አጋርነት እንዲያጤኑት ማድረጉን ዘጋርዲያን ዘግቧል።
ከወራት በፊት በአውሮፓ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ለእስር የተዳረጉት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና ሁኔታ የዚሁ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ጋዜጣው አመልክቷል።
በምዕራብ ሸዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በበኩላቸው መንግስት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽን እንደሚሰጥ ቃል ቢገባም የተደረገ ውጤታማ ውይይት አለመካሄዱን አስረድተዋል። የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽን አግኝተዋል ሲሉ አስተባብለዋል።