ዜና (የካቲት 2 ፥ 2009)
በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ የሚገኙ የአንደኛ አመት የኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ሰሞኑን በወሰዱት ፈተና አንድም ተማሪ ሊያልፍ አለመቻሉን ተከትሎ ረቡዕ በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ተቃውሞን አካሄዱ።
የዩኒቨርስቲው አስተዳደር በበኩሉ የፈተና ሂደቱ ከፖለቲካ ጋር የተገኛኘ ነው በማለት ተማሪዎቹ የጀመሩትን ተቃውሞ ለማረጋጋት መሞከሩን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ረቡዕ ረፋድ ላይ በተቀሰቀሰው በዚሁ ተቃውሞ የመማሪያ ክፍሎች መስኮቶችን መሰባበራቸውና ተማሪዎቹ ቁጣቸውን ሲያሰሙ ማርፈዳቸው ታውቋል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ተማሪዎቹ ተቃውሟቸውን እንዲያቆሙና በጥያቄያቸው ዙሪያ ምክክርን እንዲያካሄድ በጠየቁት መሰረት በተማሪዎቹና በዩኒቨርስቲው አስተዳደር በኩል ውይይት መካሄዱን ለኢሳት የደረሰ መረጃ አመልክቷል። በውይይቱ የተገኙት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ተቃውሞን ያስነሳው የፈተናው ውጤት የፖለቲካ ጉዳይ ሊሆን ይችላል የሚል ምላሽ በመስጠት ተማሪዎቹን ለማረጋጋት ሙከራ ማድረጋቸውንም ተመልክልቷል።
ፕሬዚደንቱ አቶ ጌታቸው ተፈራ ከጸረ-ሰላም ሃይሎች ጋር ተባብረው የሚሰሩ መምህራን አሉ በማለት ፈተናውን ባወጣው መምህር ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ቃል መግባታቸውን ምንጮች ለኢሳት በሰጡት መረጃ አክለው ገልጸዋል።
ይሁንና የተማሪዎቹን ተቃውሞ ተከትሎ ተማሪዎቹ ተቃውሟቸውን ቢያቆሙም በዩኒቨርስቲው አሁንም ድረስ ውጥረት መኖሩን እማኞች አስረድተዋል።
የተማሪዎች መማክርት የሚባሉና ለዩኒቨርስቲው አስተዳደር ቅርበት ያላቸው ተማሪዎችም በየተማሪዎች ክፍል እንዲሰማሩ መደረጉን ለመረዳት ተችሏል።