ኢትዮጵያ በጉለን ንቅናቄ ተቋም የተከፈቱ ትምህርት ቤቶችን ለቱርክ ለመስጠት መወሰኗን የቱርክ ባለስልጣናት ይፋ አደረጉ

ኢሳት (የካቲት 1 ፥ 2009)

በቱርክ መንግስት የቀረበን ጥያቄ ተከትሎ ኢትዮጵያ በቱርኩ ጉለን ንቅናቄ ተቋም በአዲስ አበባ የተከፈቱ ትምህርት ቤቶችን ለቱርክ ለመስጠት መወሰኗን የቱርክ ባለስልጣናት ረቡዕ ይፋ አደረጉ።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደረጉ የቱርክ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሃገሪቱ መንግስት ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀው የጉለን ድርጅት በኢትዮጵያ የተቋቋሙ ትምህርት ቤቶች ተላልፎ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የቀረበውን ይህንኑ ጥያቄ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ትምህርት ቤቶቹ በትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎችን በማያጉላላ መልኩ ህግን ጠብቆ ለማስረከብ ቃል ገብቶ እንደነበር የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በቱርክ ጉብኝትን እያደረጉ የሚገኙ የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት (ዶ/ር) ሙላቱ ተሾመ የሃገራቸው መንግስት ትምህርት ቤቶችን በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ለማስረከብ ውሳኔ ማድረጉን እንደገለጡ ዴይሊ ሳባህ የተሰኘው የሃገሪቱ ጋዜጣ አስነብቧል።

ባለፈው አመት በቱክር ተሞክሯል የተባለን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከትሎ ቱርክ ድርጊቱ በፋቱላህ ጉለን የሚመራው የጉለን ንቅናቄ እጁ አለበት በማለት ድርጅቱን በሽብርተኛ መፈረጇ ይታወሳል።

በዚሁ በአሜሪካ የሚገኙት የንቅናቄው ሃላፊ ፋቱላ ጉለን በበኩላቸው የቱርክ መንግስት በድርጅታቸው ላይ ያቀረበው ውንጀላ መሰረተ-ቢስ እንደሆነ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ቱርክ አመራሩ ተላልፈው እንዲሰጣት ለአሜሪካ ያቀረበችው ጥያቄም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ይሁንና የቱርክ ባለስልጣናት ሃገራቸው የንግድ ግንኙነት ከመሰረተችባቸው የአፍሪካ ሃገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት በመጠቀም በድርጅቱ በተለያዩ ሃገራት የተቋቋሙ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች አገልግሎቶች መስጫ ተቋማት ተላልፈው እንዲሰጧት ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ በማካሄድ ላይ መሆኗ ታውቋል።

ከአምስት አመት በፊት በኢትዮጵያ በተከፈተው የነጃሺ ኢትዮ-ተርኪሽ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት ስር ስድስት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።

ይኸው አለም አቀፍ ትምህርት ቤት ከአዲስ አበበ ከተማ ውጭ በመቀሌና አለም ገና ከተሞች ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ያሉት ሲሆን፣ ትምህርት ቤቶች ከጀማሪ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት እንደሚሰጡ የትምህርት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

በነዚሁ ስድስት ትምህርት ቤቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በትምህርት ላይ መሆናቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

የቱርክ መንግስት እነዚሁን በጉለን ንቅናቄ የተቋቋሙት ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ እንዲከፈቱ በወቅቱ ድጋፍን አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከፈት የቱርክ ዲፕሎማቶች በስነስርዓቱ ተገኝተው እንደነበርም ታውቋል።

በቱርክ የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ ኢትዮጵያ ቱርክ በሽብር ላይ የከፈተችውን ዘመቻ ለመደገፍ ሲባል ውሳኔው መተላለፉን እንደገለጸ የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ቱርክ ከቻይና እና ህንድ በመቀጠል በኢትዮጵያ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ በጨርቃጨርቅና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርታ እንደምትገኝ ይታወቃል።

ባለፈው ወር ሁለት የሃገሪቱ ባለሃብቶች ከመንግስት ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ግንባታ የወሰዱትን ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ሳይመልሱ ከሃገር መኮብለላቸው መዘገቡ አይዘነጋም። የኢትዮጵያ ግንድ ባንክ ፋብሪካውን ለመሸጥ ጨረታን አውጥቶ ይገኛል።