ኢሳት (የካቲት 1 ፥ 2009)
የፓርላማ አባላትን ጨምሮ ከሃላፊነታቸው የሚነሱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን እንዲያገኙ የሚያስችል አዋጅ ጸደቀ።
ያለምንም ተቃውሞ በፓርላማ አባላቱ የጸደቀው ይኸው አዲስ አዋጅ ሁለት የምርጫ ዘመን እና ከዚያ በላይ ያገለገሉ የምከር ቤቱ አባላት የመኖሪያ ቤት አገልግሎት እንዲያገኙ መፍቀዱ ታውቋል።
እንዲሁም አንድ የምርጫ እና ከግማሽ ያላነሰ አገልግሎት ያበረከቱ፣ በህመም በአካል ጉዳት ወይንም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከሃላፊነት ለሚነሱ ደግሞ በግልና ለቤተሰቦች ኪራይ እየከፈሉ የሚኖርበት ቤት እንደሚሰጣቸው በአዋጁ መደንገጉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በአሁኑ ወቅት ሁሉም (564 የሚሆኑት) የፓርላማ አባላት የገዢው የኢህአዴግ ተወካዮች ሲሆን፣ በአባላቱ የጸደቀው አዋጅ የጥቅማጥቅም ተካፋይ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑ ተመልክቷል።
ከሃላፊነት የሚነሱ የቀድሞ የምክር ቤት አባል ቀድሞ በነበረበት የመንግስት መስሪያ ቤት መመደብ ካልቻሉ በሌሎች መስሪያ ቤቶች ተመሳሳይ ክፍት የስራ ቦታ እንዲመደቡ በአዋጁ ተደንግጓል።
ማንኛውም የምክር ቤት አባል ከሃላፊነት ተነስቶ ጥቅማጥቅሞችን ከማግኘቱ በፊት ከዚህ አለም በሞት ቢለይ ሊከፈለው የሚገባው የመቋቋሚያ አበል፣ የስራ ስንብት ክፍያ፣ የመኖሪያ ቤት አበልና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ለቤተሰብ እንዲሰጥ መፍቀዱንም ለመረዳት ተችሏል። ይሁንና፣ ሌሎች ጥቅማ-ጥቅሞች የተባሉት በዝርዝር ሳይጠቀሱ ቀርተዋል።
ከፓርላማ አባላቱ በተጨማሪ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች እንዲያገኙ በአዋጁ የተደነገገ ሲሆን፣ በጉዳዩ ዙሪያ ግን የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።
ለባለስልጣናት እና ለፓርላማ አባላቱ የቀረበው ይኸው ልዩ ጥቅማጥቅም ተሿሚዎች ከሃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ ምን እንሆናለን የሚለውን ስጋት ለማስቀረት ያለመ ነው ተብሏል። መንግስት ለዚሁ ጥቅማጥቅም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ እንደሚያደርግ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፣ የፓርላማው የህግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊሰጥ የተወሰነው ጥቅማጥቅም በመንግስት በጀት ላይ የተለየ ተፅዕኖን የማይፈጥር ነው ሲል አስታውቋል።