በምስራቅ አፍሪካ የርሃብ አደጋው እንደ አዲስ ማገርሸቱን ተከትሎ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል ሲል የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት አስጠነቀቀ።

ጥር ፴ (ሠላሳ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቀጠናው በተከሰተው አዲሱ ድርቅ ምክንያት ቁጥራቸው 11.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ለከፍተኛ የርሃብ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል። እንደ ድርጅቱ መግለጫ በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ አፋጣኝ የረድኤት እርዳታ ጠባቂ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን እና የድርቁ ደረጃ በርሃብ መለኪያ Integrated Phase Classification (IPC) ከሶስት ነጥብ በላይ መሆኑን አስታውቋል። በሶማሊያ 2.9 ሚሊዮን፣ በኬንያ 2.7 ሚሊዮን፣ በኢትዮጵያ 5.6 ሚሊዮን አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ጠባቂዎች ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያ በድርቁ ተጋላጭ ከሆኑት የቀጠናው አገራት ከፍተኛውን ቁጥር ትወስዳለች። በተጨማሪም ደቡብ ሱዳን 5 ሚሊዮን የድርቅ ተጠቂዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱ ቁጥራቸው 1.2 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናዊያን ዜጎች በምግብ እጥረት ተጠቂ ሆነዋል።