የዘንድሮው የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌስቲቫል በዋሽንግተን ሲያትል ከተማ እንደሚካሄድ ተገለጸ

ኢሳት (ጥር 30 ፥ 2009)

በየአመቱ በሰሜን አሜሪካ በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው የዘንድሮው የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል የፊታችን ሃምሌ በዚሁ በአሜሪካ ዋሽንግተን ግዛት ሲያትል ከተማ እንደሚካሄድ መወሰኑን አዘጋጆች አስታወቁ።

ለ34ኛ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማሰባሰብ የሚካሄደው ይኸው አመታዊ በዓል በፈረንጆቹ ከሃምሌ 2 እስከ 8 2017 ድረስ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የባለፈው አመት ዝግጅት በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ የዘንድሮውን በዓል ለማስተናገድ የቴክሳስ ግዛት ጥያቄ አቅርቦ እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል።

ለ34ኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚሁ አመታዊ የስፖርትና የባህል ፌስቲባል ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና እንግዶች እንዲሁም ከተለያዩ የአለማችን ክፍል የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አመታዊ ፌስትባሉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከማሰባሰቡ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ለውጭ ሃገር ተወላጆች ለማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖን እያበረከተ እንደሚገኝ የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

በተያዘው አመት ሃምሌ ወር በዋሽንግተን ግዛት ሲያትል ከተማ የሚካሄደው ዝግጅት በስፍራው እንደሚከናወን ሲወሰን በ13 አመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የሰሜን አፍሪካ የስፖርት ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫው አመልክቷል።