ለስኳርና ኤሌክትሪክ ግንባታዎች ከይዞታቸው እንዲነሱ የተደረጉ አርሶ አደሮች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ተነገረ

ኢሳት (ጥር 26 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ሶስት ክልሎች ለስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ እና ለኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶች ከይዞታቸው እንዲነሱ የተደረጉ ወደ ሶስት ሺ አካባቢ አርሶ አደሮች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ተነገረ።

በኦሮሚያ ክልል አርጆ ዴዴሳ፣ በአማራ ክልል ጣና በለስ የስኳር ልማት እንዲሁም በደቡብ ክልል ጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶች ከቀያቸው እንዲነሱ የተደረጉት ወደ 3ሺ አካባቢ አርሶ አደሮች ምትክ መሬትና ካሳ ሳይሰጣቸው አመታት መቆጠሩን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል።

ከአርሶ አደሮቹና ከተለያዩ አካላት ሲቀርብ የነበረን ቅሬታ ተከትሎ ጥናትን ያካሄደው ኮሚቴ በኦሮሚያ አርጆ ዴዴሳ የስኳር ፕሮጄክት ከ1ሺ 600 በላይ አርሶ አደሮች ምትክ ቦታም ሆነ ካሳ ሳይሰጣቸው ከይዞታቸው እንዲነሱ መደረጉን ለፓርላማ ባቅረበው ሪፖርት አስረድቷል።

ወደ 737 አካባቢ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ንብረታቸው ሳይገመት እንዲሁም ለይዞታቸው ምትክ መሬት ባለመሰጠቱ ሳቢያ በላስቲክ መጠለያ እንዲቆዩ መደረጉን መንግስታዊ ኮሚቴው ለፓርላማ መግለጹን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታም 220 አካባቢ የሚሆኑ አርሶ አደሮች በዚሁ ክልል የቅድሚያ ምትክ መሬት እና ተገቢው ካሳ ሳይሰጣቸው የግድብ ውሃ ደርሶባቸው ከይዞታቸው መፈናቀላቸው ተመልክቷል።

በዚሁ የስኳር ፕሮጄክቶች የተወሰኑ አርሶ አደሮች ከመኖሪያ አካባቢያቸው 60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ምትክ ቦታ ቢሰጣቸውም አርሶ አደሮቹ ዘጠኝ ሰዓት ያህል በእግር እንዲጓዙ መገደዳቸውን በችግሩ ዙሪያ የተካሄደው ጥናት ገልጿል።

በአማራ ክልል የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጄክት በተመሳሳይ ሁኔታ 1994 አርሶ አደሮች ለችግር የተጋለጡ ሲሆን፣ የውሃ የመስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ችግሩ ከየክልሎቹ መንግስታት ጋር የጋራ መርሃ ግብር ባለመዘጋጀቱ ነው ሲል ምላሽን ሰጥቷል።

በቅርቡ በስኳር ፕሮጄክቶች ግንባታ ሳቢያ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበት የነበረው የስኳር ኮርፖሬሽን በበኩሉ ለተፈናቃይ አርሶ አደሮች የሚከፈላቸው ካሳ ተመን ስላልቀረበለት ክፍያ ሊፈጸም አመለቻሉን አስታውቀዋል።

መንግስታዊ ድርጅቶቹ ለችግሩ ዕርስ በርስ ቢወነጃጀሉም ከ2ሺ 800 በላይ አርሶ አደሮች በከፋ ችግር ለአመታት መቆየታቸውን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስረድቷል።

በግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት የዱር እንስሳትና በአካባቢው ያሉ ቅርሶች እንዲፈርሱ መደረጉንም ጥናቱ አመልክቷል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል እና የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን ተጠያቂ ናቸው ብለዋል።

የስኳር ፕሮጄክቶቹ በተጀመሩ ወቅት በርካታ አርሶ አደሮች የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብናል ሲሉ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲገልፅ መቆየታቸው ይገልጻል።

የስኳር ኮርፖርሬሽን ከተለያዩ አበዳሪ አካላት በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ብድርን ወስዶ የስኳር ግንባታን ቢጀምርም ከአምስት አመት በኋላ አንድም ፋብሪካ ወደ ምርት አለመግባቱ ሲገልፅ ቆይቷል።