በደሴ ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው ስብሰባ የጸጥታ ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆኖ ቀረበ

ጥር ፳፭ (ሃያ አምስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተለያዩ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናትን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢህአዴግ አባላት እየተሳተፉበት ባለው ስብሰባ የጸጥታ ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል። በተለያዩ መድረኮች በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ በክልሉ የሚታየው የጸጥታ ሁኔታ በአባላት ዘንድ ተደጋግሞ የቀረበ ጥያቄ ነበር።
በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ጥሩ እንደሆነ ገለጻ የሰጡት የመድረኩ መሪዎች፣ ይህንን እንዲያረጋግጡ ከወልቃይት፣ አርማጭሆ እና ቋራ የመጡ አርሶአደሮችን በእማኝነት እንዲያስረዱ አድርገዋል። አርሶአደሮቹም በአካባቢያቸው ሙሉ በሙሉ ሰላም መስፈኑን፣ የጥይት ጩኸት የለም ሲሉ ለተሰብሳቢው ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ ሌላ ተሰብሳቢ “ ህዝብና መንግስት በአሁኑ ሰአት ተለያይተዋል፣ ለመሆኑ ከህዝቡ ጋር የምንታረቀው መቼ ነው፣ መፍትሄውስ ምንድነው?” የሚል ጥያቄ ያነሳ ሲሆን፣ ጥያቄው የመድረክ መሪዎችን አበሳጭቷል። መድረክ መሪው በቁጣ ፣ “ይህንን ጥያቄ የጠየቅኸው ሰው በቀ ግንዛቢ ስለሌለህ ነው፣ ስትደራጅ ያን ጊዜ ይገባሃል” በማለት ለጠያቂው መልስ ሰጥተዋል።
ተቀናሽ የሰራዊት አባላት በበኩላቸው “እስከዛሬ ሳታስታውሱን አሁን ችግር ሲፈጠር ነው ወይ የምታስታውሱን ?” በማለት የጠየቁ ሲሆን፣ መድረክ መሪዎችም ፣ “ አዎ እስከዛሬ ረስተናችሁዋል፣ አሁን ልዩ ትኩረት ማድረግ ጀምረናል፣ እንክብካቤ እናደርግላችሁዋል ፣ ከእኛ ጋር አንድ ሁናችሁ በጋራ እንሰራለን” የሚል መልስ ሰጥተዋል።
ሌላ ተሰብሳቢ ደግሞ “ ለመሆኑ መቼ ነው ለህዝብ ትችት የምንቀርበው?” በማለት የጠየቀ ሲሆን፣ “ እኛ ለህዝብ ትችት የምንቀርበው በቅድሚያ ከአባሎቻችን ጋር መግባባት ስንፈጥር ነው” የሚል መልስ ተሰጥቷል።
በስብሰባው ወቅት ታማኝ ለሚባሉት የኢህሃዴግ አባላት <፡ተመላሽ ሰራዊት አባላትን እንድትንከባከቡ፣ በእያካባቢያችሁ ያሉ የተመላሽ ሰራዊትን ብዛት እንድታሳውቁ፣ የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅማችሁ አዳዲስ ሰልጣኝ ወታደሮችን እንድትመለምሉ፣ እንዲሁም ኢህአዴግ ከሌለ እናንተም እንደማትኖሩ አውቃችሁ ሌት ተቀን ድርጅታችሁን ጠብቁ” መባላቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ጥር 22 የተጀመረው ስብሰባ በነገው ዕለት ይጠናቀቃል።