ኢሳት (ጥር 24 ፥ 2009)
በፌዴራልና በሶማሌ ክልል አስተዳደር ድጋፍ ይደረግላቸዋል የተባሉ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልልና የብሄሩ ተወላጆች ላይ ግድያን ጨምሮ የንብረት ዘረፋና ወረራን እየፈጸሙ እንደሚገኝ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ረቡዕ ይፋ አደረገ።
ከሁለት ወር በፊት ጀምሮ በተለይ በክልሉ በምስራቅ ሃረርጌ፣ ባሌና ቦረና ዞኖች ውስጥ መፈጸሙ የጀመረው ይኸው ድርጊት ያለማንም ከልካይ አሁንም ድረስ ተጠናክሮ መቀጠሉን ፓርቲው በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ባለፈው ሳምንት የፌዴራል መንግስት የኦሮሚያ ክልልን ከሶማሌ ክልል ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ግጭት ተቀስቅሶ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እንደገለጸ መዘገባችን ይታወሳል።
ይሁንና የፌዴራል መንግስት በዚሁ ግጭት የደረሰውን የሰውም ሆነ የንብረት ጉዳት በዝርዝር ከመግለጽ የተቆጠበ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ መግለጫን ያወጣው ኦፌኮ በአካባቢው እየተፈጸመ ያለው ግድያ እንዲሁም ንብረት የመዝረፍና የወረራ ድርጊቱ ቀጥሎ እንደሚገኝ አመልክቷል።
ድርጊቱን እየፈጸሙ ያሉት አካላት የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የመንግስት ታጣቂዎች ናቸው ያለው ፓርቲዎች በፌዴራል በሶማሌ ክልል አስተዳደሮች የሚደገፉ መሆናቸውን አክሎ አስታውቋል።
ከጥቂት አመታት ወዲህ ጀምሮ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ግድያና አፈና ተጠናክሮ መቀጠሉን ያወሳው ፓርቲው በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ የብሄሩ ተወላጆች በእስር ላይ እንደሚገኙ አክሎ ገልጿል።
የፓርቲው አመራር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥሰዋል ተብለው ከአንድ ወር በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
በአመራሩ ላይ ምርመራን እያካሄደ እንደሆነ የሚገልጸው ፖሊስ በቅርቡ ለሶስተኛ ጊዜ የ28 ቀን የተጨማሪ ጊዜ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ፈቃድ እንደተሰጠው ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ የመለክታል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ፖሊስ የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ለመመስረት ያስችለኛ ብሎ የሚያካሄደውን ወንጀል እንዳልፈጸሙ ለፍርድ ቤት አስረድተዋል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለአንድ አመት ያህል ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ዘልቆ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ አንድ ሺ አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ተገድለው በሺዎች የሚቆጠሩ ዳግም ለእስር መዳረጋቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊነት የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት የአዋጁን መውጣት ተከትሎ ከ24ሺ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንና ወደ ዘጠኝ ሺ የሚሆኑ መለቀቃቸውን ባለፈው ወር ማስታወቁ ይታወሳል።