ኢሳት (ጥር 24 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ በአለማችን በሰብዓዊ መብት አያያዛቸውና በዴሞክራሲ ስርዓታቸው ነጻ ያልሆኑ ተብለው ከተፈረጁ 25 ሃገራት መካከል አንዷ ሆና መፈረጇን መቀመጫውን በዚሁ በአሜሪካ ያደረገ አንድ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋም ይፋ አደረገ።
የ2016 አም አመታዊ ሪፖርቱን ለንባብ ያበቃው ፍሪደም ሃውስ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተለይ ባለፈው የፈረንጆች አመት ከመቼውም ጊዜ የተባባሰ ሆኖ መመዝገቡን አስታውቋል።
በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች ተቀስቅሶ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት የሃይል ዕርምጃ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ አንድ ሺ አካባቢ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።
በመገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ድረገጾች ላይ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጠናከረው መቀጠላቸውን ያወሳው ፍሪደም ሃውስ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ስርዓት ምንም አይነት መሻሻልን ሳያሳይ ባለፈው አመት ከዜሮ በታች ሶስት ነጥብ ማስመዝገቡን አመልክቷል።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2016 አም በተካሄደ ጥናትም ሃገሪቱ ነጻ ያልሆኑ ሃገራት መካከል አንዷ ሆና ተቀምጣለች።
የመን፣ ኒጀር፣ ሞዛምቢክ፣ ሌሶቶ፣ እና ሃንጋሪ ከኢትዮጵያ ዕኩል ከዜሮ በታች ሶስት ነጥብ በመያዝ በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው የሰላ ትችት የቀረበባቸው ሲሆን፣ ቱርክ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሊቢያና ኒካራጓ ከዜሮ በተቻ 15, 10 እና 7 ነጥብን እንደቅደም ተከተላቸው አስመዝግበዋል።
የኢትዮጵያ፣ ቻይና፣ ሆንግ ኮንግ፣ ሞዛምቢክ ፊሊፒንስ፣ ቱርክ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዛምቢያ፣ እና ፖላንድ ደግሞ ባለፈው አመት የሰብዓዊ መብት አያያዛቸውና የዴሞክራሲ ስርዓታቸው ማሽቆልቆልን ካስመዘገቡ ሃገራት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በሪፖርቱ አስፍሯል።
በጥናቱ ከተካተቱ 195 የአለማችን ሃገራት መከከል 45 በመቶ የሚሆኑን ነጻ ሃገር ተብለው የተቀመጡ ሲሆን፣ 30 በመቶ የሚሆኑት ደግምሞ በከፊል ነጻ ሃገር ለመባል በቅተዋል።
ለተከታታይ 11ኛ አመት የአለም ነጻነት ተዳክሞ መቀጠሉን ያስታወቀው ፍሪደም ሃውስ 36 ሃገራት ብቻ መሻሻልን እንዳስመዘገቡ አክሎ ገልጿል።
ሶሪያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ እና ኡዝቤኪስታን የከፋ ነጥብን አስመዝግበዋል ተብለው በሪፖርቱ ተቀምጠዋል። በቅርቡ በሃገሪቱ ለ50 አመታት ያህል የቆየውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከአማጺ ቡድን ጋር ስምምነት የደረሰችው ኮሎምቢያ ነጻ ለመባል የበቃች ብቸኛ አዲስ ሃገር መሆኗም ታውቋል።