ጥር ፳፫ (ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደሴ ከተማ ከጥር 22 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ “ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ” በሚል ሰበብ የፌደራል ባለስልጣናት እና ሌሎች የኢህአዴግ አባላት በተገኙበት በመካሄድ ላይ ባለው ስብሰባ ላይ፣ ገዢው ፓርቲ በአማራ ክልል በተለይም በጎንደርና በጎጃም ተነስቶ የነበረውን ህዝባዊ አመጽ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ለተሰብሳቢዎች ቢናገሩም፣ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ያንን እንደማያመልክት ተሰብሳቢዎች ተናግረዋል።
ከፌደራል ባለስልጣናት የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳን ጨምሮ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ባለቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ እና በርካታ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዲኤታዎች፣ የ32 ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የተማሪዎች የሊግ አባላት ተወካዮች፣ ከትምህርትና ከጸጥታ ዘርፍ ቁልፍ የተባሉ ሰዎች ፣ የሴክተር መስሪያ ቤት ተወካዮች፣ ብዛት ያላቸው የደህንነት ሰራተኞች በስብሰባው እየተሳተፉ ሲሆን፣ ከተማዋ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ወታደሮችና የፌደራል ፖሊስ አባላት ትጠበቃለች።
የደሴ ወጣቶች በአንድ ተሰብሳቢ ላይ ወይም በተሽከርካሪዎች ላይ ድንጋይ ቢወረውሩ የከተማው ፖሊስ ተጠያቂ እንደሚሆን የተሰጣቸውን ትእዛዝ ተከትሎ፣ ፖሊሶቹ ህዝቡን በከፍተኛ ወከባ ውስጥ ጥለውታል። ለ5 ቀናት በሚደረገው ስብሰባ 5 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ስብሰባ በወሎ ዩኒቨርስቲ፣ መምህራን ኮሌጅ፣ ወ/ሮ ስህን ቴክኒክ ኮሌጅ እና ሩቅያ አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል።
ስብሰባው በትምህርት ጥራት ዙሪያ ለመምከር የሚል ርእስ ቢሰጠውም ዋናው አላማው በቅርቡ በአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች የተያየውን ህዝባዊ አመጽ መገምገም ነው። ዋናው ግምገማ ዛሬ እንደሚጀመር የሚጠበቅ ሲሆን፣ እስካሁን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተደረጉት ስብሰባዎች የፌደራል ባለስልጣናት በጎንደርና በጎጃም የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ ገዢው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል። “በአሁኑ ሰአት በሰሜን አካባቢ አንድም የጥይት ድምጽ አይሰማም ያሉት ባስልጣናቱ ወንበዴዎች ተመትተዋል፣ ብዙዎችም እጃቸውን ሰጥተዋል” ብለዋል። ይሁን እንጅ ተሰብሳቢዎች ይህንን ለመቀበል እንደከበዳቸው ምንጮች ገልጸዋል። “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሳይነሳ፣ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃቶች እየተፈጸሙ፣ በቅርቡ በባህርዳርና ጎንደር የቦንብ ፍንዳታዎች ደርሰው፣ መኪኖች እየተቃጠሉና የተወሰኑ አካባቢዎች ለተሽከርካሪዎች ዝግ ሆነው እንዴት እንቅስቃሴውን ተቆጣጥረነዋል ይባላል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
በክልሉ የሚገኙ ወጣቶች ችግር ላይ መውደቃቸውን፣ በትምህርቱ መግፋት ባለመቻላቸው ለችግር መደራጋቸውንና ይህም የጸጥታውን ሁኔታ እንደሚያደፈርሰው ሃሳቦች ተሰንዝረዋል።” በኩታ በር ወረዳ ውስጥ ማትሪክ ፈተና ከወሰዱት 300 ተማሪዎች መካከል ማለፍ የቻሉት 4 ብቻ ናቸው። ጠለላ ወረዳ ውስጥ ደግሞ ከ640 ተፈታኝ ተማሪዎች ማለፍ የቻሉት 140 ብቻ “ ናቸው ያሉት ተሰብሳቢዎች፣ ትምህርት ሞቷል፣ ልጆችም እየተማሩ አይደለም” በማለት የችግሩን ውስብስብነት ገልጸዋል።
በወሎ ዩኒቨርስቲ ተቀስቅሶ የነበረውን ግጭት አስመልክቶ በተማሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የፌደራል ባለስልጣናት ያቀረቡትን ሃሳብ ተሰብሳቢዎች ችግሩን ይበልጥ የሚያወሳስበው ነው በማለት ተቃውመዋል።
አረበኮ አካባቢ ደግሞ በኢንጂነሪንግ የተመረቁት ሙሃመድ ስዩምና ጀማል ስዩምን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች አመጽ አስነስታችሁዋል ተብለው ታስረዋል።
በሌላ በኩል በባህርዳር ከተማ የፌደራል ፖሊሶች በመግቢያና መውጫ ቦታዎች ላይ ፍተሻ ሲያካሂዱ መዋላቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ የመለክታል።