ኢሳት (ጥር 23 ፥ 2009)
በቅርቡ በጋምቤላ ክልል በአንድ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ተፈጽሞ ከነበረው ጥቃት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 20 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ማክሰኞ አስታወቀ።
ከአንድ ወር በፊት በክልሉ ኢታንግ ልዩ ወረዳ አካባቢ 40 መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አውቶቡስ በተፈጸመበት ጥቃት አምስት ሰዎች በተከፈተባቸው የተኩስ ዕርምጃ መሞታቸው ይታወሳል።
በዚሁ ጥቃት በትንሹ ስምንት ተሳፋሪዎች ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበርም ፖሊስ በወቅቱ ገልጿል።
የክልሉ ፖሊስ ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ከአንድ ወር በላይ ፍለጋን ሲያካሄድ ከቆየ በኋላ 20 ተጠርጣሪዎችን ከቀናት በፊት በቁጥጥር ስር ሊያውል መቻሉን አመልክቷል።
የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ፖል ቱት ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በኤርትራ መንግስት በመሰልጠንና በህገ-ወጥ መንገድ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ነው ሲሉ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ይሁንና ሃላፊው ተጠርጣሪዎቹ መቼ በቁጥጥር ስር እንደዋሉና ታጥቀው ነበር ስላሉት መሳሪያ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የተወሰኑት እጃቸውን በሰላም ሰጥተዋል ሲሉ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አክለው ገልጸዋል።