ኢሳት (ጥር 23 ፥ 2009)
5 ቢሊዮን ብር ያህል የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ እንደባከነበት የተገለጸው የጋምቤላ ዕርሻ ኢንቨስትመንት እንደገና ተጨማሪ ብድር እንዲለቀቅለት ተወሰነ። ከፍተኛ የሃገር ሃብት ባክኖበታል በተባለው በዚሁ ኢንቨስትመንት ግለሰቦችና ባለስልጣናት እንደሚጠየቁ ሲጠበቅ፣ ተጨማሪ ብድር እንዲለቀቅ መወሰኑ አነጋጋሪ ሆኖ መገኘቱንም መረዳት ተችሏል።
በጋምቤላ ክልል በተካሄደው የእርሻ ኢንቨስትመንት ከየአቅጣጫው የተነሳበትን ወቀሳ ተከትሎ 15 አባላት ያህል ያሉት ኮሚቴ ተዋቅሮ ምርመራ ሲያካሄስ መቆየቱም ይፋ ሆኗል። በጠ/ሚ/ሩ ቢሮ የተዋቀረውና በቀድሞ የውሃና ኤነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ የተመራው ኮሚቴ ባካሄደው ምርማራ ከፍተኛ የሃገር ሃብት መባከኑን በዝርዝር ማጋለጡ ይታወሳል።
በህዳር ወር 2009 ይፋ የሆነውና 63 ገጾች ያሉት የጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው፣ ባለሃብቶች ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ንግድ ባንክ የወሰዱት ገንዘብ 4.9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ መልማት ከሚገባው 630 ሺ ሄክታር መሬት ያለሙት 76 ሺህ ሄክታር ብቻ ነው። መሬት ከተረከቡት 623 ባለሃብቶች የእርሻ መሳሪያ ያላቸው 226 ብቻ ሲሆኑ ፣ 397ቱ የእርሻ መሳሪያ ሳይኖራቸው በእርሻ ስራ የተሰማሩ መሆናቸው ተመልክቷል።
እነዚህ በጋምቤላ እርሻ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩት በብድር ከወሰዱት 4.9 ቢሊዮን ብር ባሻገር ፣ የቀረጥ ነጻ መብትን በመጠቀም ብረት፣ ተሽከርካሪ ወዘተ በማስገባት ለሌላ ጥቅም ማዋላቸውም በሪፖርቱ ተዘርዝሯል። ብድሩን ከወሰዱት ውስጥ 29ኙ ግለሰቦች ገንዘቡን ይዘው የት እንደደረሱ እንደማይታወቅም በጥናት ሪፖርቱ ተመልክቷል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ 4.9 ቢሊዮን ብር የባከነበት የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመንት፣ ባለሃብቶቹንና የባንክ ሃላፊዎቹን ተጠያቂ እንደሚያደርግ በወቅቱ ቢጠበቅም፣ የልማት ባንኩን ፕሬዚደንት ከስልጣን ከማንሳት ውጭ የተወሰደ ዕርምጃ የለም።
የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) አባል የሆኑት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ኢሳያስ ባህረ ሪፖርቱን ተከትሎ በህዳር 2009 ከስልጣናቸው ሲነሱ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዢ የነበሩት አቶ ጌታሁን ናና ተከትለዋቸዋል።
አዲሱ ተሿሚ በነበረው ሁኔታ መደንገጣቸው በወቅቱ ቢገለጽም፣ በእርሳቸውም አመራር ብድሩ እንዲለቀቅ ተወስኗል።
የጥናቱ ስራ በየካቲት 2008 መጀመሩን ተከትሎ ከመጋቢት 2008 ጀምሮ ታግዶ የነበረው የልማት ባንክ ብድር ከጥር 24 ፥ 2009 ጀምሮ እንዲቀጥል መወሰኑን አዲስ አበባ የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ አረጋግጧል።
ሆኖም ብድሩ እንደገና ቢለቀቅም ቁጥጥር በተመላበት አሰራር እንዲፈጸም መወሰኑን እንዳስደሰታቸው አቶ ጽጌ ህይወት መብራህቱ እና አቶ የማነ ሰይፉ የተባሉ ግለሰቦች ለሪፖርተር ተናግረዋል።
አቶ የማነ ሰይፉ የጋምቤላ ክልል ዕርሻ ኢንቨስትመንት ማህበር ፕሬዚደንት ሲሆኑ ይህ ማህበር ሙሉ በሙሉ በትግራይ ተወላጆች የታያዘ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
የዚሁ ማህበር ፕሬዚደንት አቶ የማነ ሰይፉ፣ የጥናት ቡድኑን የምርመራ የአሰራር ሂደት በመቃወም ህዳር 14 ቀን 2009 መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል።
“የትግራይ ተውላጆች ናቸው በሚል የእርሻ ኢንቨስትመንታችን ኢላማ ውስጥ ገብቶ በቢሮክራሲው እንዲዳከም እየተደረገ ነው” በሚል ርዕስ ባወጡት በዚህ መግለጫ “ለጥቂት የትግራይ ተወላጆች የልማት ባንክ ያለመያዣ ገንዘብ የሰጣቸው፣ ለግብርና ብለው የወሰዱትንም ገንዘብ አዲስ አበባ ፎቅ የስሩበታል” በሚል ዘመቻ ተከፍቶብና በማለት በጠ/ሚ/ሩ ቢሮ የተዋቀረውን ኮሚቴ የወቀሱ ሲሆን፣ የእኛና የሃገር ጠላቶች ናቸው በማለት ወንጅለዋቸዋል። በኢሳት የተከፈተብንን ዘመቻ አጠናክረዋል በማለት ከሰዋል።
በጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመንት ከተሰማሩት የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች 75 በመቶ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን መቀመጫውን አሜሪካ ካሊፎርኒያ ያደረገው የኦክላንድ ኢንስቲቲዩት ያጋለጠው ከ5 አመት በፊት ሲሆን፣ የትግራይ ተወላጆች በጋምቤላ ዕርሻ ኢንቨስትመንት ማህበር ስም ማረጋገጫ የሰጠበት ሲሆን፣ ሰብሳቢው የማነ ሰይፉም በጉዳዩ ዙርያ ባለፈው ህዳር ለቪኦኤ በሰጡት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
በአጋጣሚ ሆነ ጋምቤላ ውስጥ ካለው ኢንቨስትመንት የትግራይ ትወላጆች ይበዛሉ ማለታቸውም በጽምፅ ተላልፏል።