ኢሳት (ጥር 22 ፥ 2009)
ባለፈው ስድስት ወራቶች ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ 14 ሺ የንግድ ተቋማት የንግድ ፈቃዳቸውን በተለያዩ ችግሮች እንደመለሱ ተገለጸ።
እነዚሁ በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ ተሰማርተ የነበሩ ድርጅቶች ህገወጥ ንግድ መበራከት፣ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የልማት እንቅስቃሴ ደካማ የንግድ ስርዓት ኣንዲሁም የቤት ዋጋ ንረት ከገበያ እንዲወጡ ጫና እንዳደረሰባቸው ማስታወቃቸውን ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል።
በከተማዋ እየተስተዋሉ ያሉ እነዚህን ችግሮች ተከትሎ በየዕለቱ 70 የሚሆኑ የንግድ ተቋማት የንግድ ስራ ፈቃዳቸውን ለአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ እየመለሱ መሆናቸው ተመልክቷል።
የንግድ ድርጅቶቹ ፈቃዳቸውን ለመመለስ በመንግስት የግብር ገቢና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።
በተለያዩ አካላት ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ያልተቀረጡ ሸቀጣሸቀጦች በንግድ ስራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አቶ ኤርሚያስ ሃይሌ የተባሉ በኮሞፒውተር ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ ለጋዜጣው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ተወካይ የሆኑት ምትኬ እንግዳ በበኩላቸው ቢሮው ህገወጥ ንግዱን ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም ችግሩ ሊቀንስ እንዳልቻለ ተናገረዋል።
ባለፈው አመት በተመሳሳይ ችግሮች 26ሺ 860 የንግድ ተቋማት ፈቃዳቸውን መልሰው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ባለው ሂደት ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተመልክቷል።
የንግድ ፈቃዳቸውን እየመለሱ ያሉ የንግድ ድርጅቶች መንግስት ለችግሮቹ መፍትሄን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በአዲስ አበባ ከተማ 261ሺ 401 የንግድ ድርጅቶች በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ታውቋል።