አሜሪካ ከጎረቤት ሜክሲኮ ጋር የሚያዋስናትን 3ሺ 200 ኪሎሜትር ድንበር ለመከለል 15 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል ተባለ

ኢሳት (ጥር 19 ፥ 2009)

አሜሪካ ከጎረቤት ሜክሲኮ ጋር የሚያዋስናትን 3ሺ 200 ኪሎሜትር ድንበር ለመከለል ወደ 15 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንዲሚያስፈልጋት ተገለጸ።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜያቸው የገቡት ይኸው ቃል በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲደርግና ወጪው በሜክሲኮ እንደሚሸፈን ሃሙስ ይፋ አድርገዋል። ሜክሲኮ በበኩሏ ዕርምጃውን በመቃወም ወጪውን በምንም ሁኔታ እንደማትሸፍን ምላሽን ሰጥታለች።

የሁለቱ ሃገራት መሪዎች በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የፊታችን ሳምንት ለመገናኘት ቀጠሮን ይዘው የነበረ ቢሆንም፣ በተፈጠረው አለመግባባትን የሜክሲኮውን ፕሬዚደንት ጉብኝታቸውን እንደሰርዙ አስታውቀዋል።

ፕሬዚደንቱ ኢንሪኮ ፔኒኣ-ኒኤ’ቶ ሃገራቸው ሊገነባ የታሰበውን አጥርና ግንብ በምንም አይነት ድርድር ወጪውን ለመሸፈን ፍላጎት እንደሌላት ምላሽን መስጠታቸውን አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሜክሲኮ ለድንበር ማካለሉ ወጪን የማትሸፍን ከሆነ ከሃገሪቱ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የተለያዩ የንግድ ቁሳቁሶች ላይ የ20 በመቶ አዲስ የታክስ አገልግሎት ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

አሜሪካ ይህንኑይ የታክስ አገልግሎት ተግባራዊ በማድረጓም በአመት 10 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ገቢ እንደሚገኝ የፕሬዚደንቱ ቃለ አቀባይ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

ባለፈው የፈረንጆች 2015 አም ሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የላከችው የንግድ ገቢ 316 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ሲሆን፣ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ የ50 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ልዩነት እንዳለው ተመልክቷል።

ይሁንና አሜሪካ ለመጣል ያሰበችው የ20 በመቶ የታክስ አገልግሎት ክፍያ ከሜክሲኮ የሚገቡ የተለያዩ ቁሳቁሶች ዋጋቸው እንዲንር የሚያደርግ መሆኑን የተለያዩ አካላት ገልጸዋል። ዕርምጃውም በሜክሲኮ ንግድ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖን ያሳድራል ተብሎ ይጠበቃል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት የያዙት ይኸው አጨቃጫቂ አቋም በቅርቡ ለምክር ቤት ቀርቦ ምክክር ይካሄድበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ለመረዳት ተችሏል።

የአሜሪካው አዲስ ፕሬዚደንት ሶስተኛ የንግድ ሸሪክ ከሆነችው ሜክሲኮ ጋር በድንበርና በኢኮኖሚ ዙሪያ የያዙት አቋም ሊጤን የሚገባው እንደሆነ የተለያዩ የፓርቲ አባላት በመግለጽ ላይ መሆናቸው ሲኤን ኤን ዘግቧል። አሜሪካ ለበርካታ አመታት ወደ ሃገሯ የሚገቡ ሸቀጣሸቀጦች ላይ የቀረጥ ክፍያ ተግባራዊ አለማድረጓ ፍትሃዊ አለመሆኑን የፕሬዚደንቱ አማካሪዎች ይገልጻሉ።

በአሜሪካ እና በሜክሲኮ መካከል ተፈጥሯል የተባለው የኢኮኖሚ ጦርነት በሂደት ሌሎች ሃገራት ላይም የንግድ ተፅዕኖን ያሳድራል ተብሎ መሰጋቱን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።