ጥር ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ፣ ኦሮምያና ደቡብ ክልሎች “ጥልቅ ተሃድሶ” በሚል የሚደረጉ ስብሰባዎች የመንግስት ስራ እንዲቆም በመድረጉ ህዝቡ አገልግሎት ማግኘት አልቻለም። በአብዛኛው ቦታዎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች በመዘጋታቸው አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፣ አንዳንድ ተገልጋዮች “ ምንም ለውጥ በማያመጣ ስብሰባ “ እየተንገላቱ መሆኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል በሚካሄደው ስብሰባ፣ ሰራተኞች የአሁኑ ስብሰባ ከአሁን በፊት ከተደረጉት ስብሰባዎች የተለየ አለመሆኑን ገልጸው፣ ከበላይ አመራሮች ጀምሮ በፓርቲው ውስጥ ጠንከር ያለ ንግግር የሚናገሩትንና ለበላይ አመራሮች ተገዥ ባለመሆን መድረክ ላይ ሃሳብ የሚያራምዱትን አመራሮች ከማስወገድ ባለፈ፣ ለህብረተሰቡ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ገለልተኛ አመራሮች አለመመረጣቸው ከህዝብ ይልቅ የፓርቲውን ህልውና ለመጠበቅ የሚጥር መንግስት መሆኑን እንደሚያሳይ ለኢሳት ተናግረዋል።
በኦሮምያ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ሰራተኞች ከፌደራል ተዘጋጅቶ የመጣውን የስራ መገምገሚያ ሰነድ ፣ “ሰራተኛውን እርስ በርስ የሚከፋፈል፣ በሰራተኞች መካከል አለመማመንን የሚፈጥር ነው” በማለት ተችተውታል።
በአዲሱ የሰራተኞች የመገምገሚያ መስፈርት መሰረት አብዮታዊ ዲሞክራሲን መቀበልና በሃይማኖት ጉዳይ ላይ የከረረ አቋም አለማሳየት ከፍተኛ ነጥብ ያሰጣሉ።
አዲሱ የመገምገሚያ ነጥብ ሰራተኛውን ሙሉ በሙሉ ለኢህአዴግ አስተሳሰብ ታማኝ እንዲሆን የሚያደርገው ነው።