በአርባምንጭ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ተከሰ

ጥር ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ በሚኖርባት የአርባምንጭ ከተማ ከፍተኛ የውሃ እጥረት መከሰቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከተማዋ 50ኛ አመቷን ባከበረችበት ወቅት ህዝቡ ባቀረበው አቤቱታ የከተማዋን የውሃ ችግር ለመቅረፍ በሚል 86 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ከተካሄድና በርካታ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ከተቀበሩ በሁዋላ፣ የሚከታተላቸው አካል በመጥፋቱ ስራው መቋረጡን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ በከተማው ያለው የውሃ እጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ በመባባሱ ለከፍተኛ ችግር ተደርገዋል። ለፕሮጀክቱ መቋረጥና ለገንዘቡ መባከን ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው ሰዎች ከመጠየቅ ይልቅ አንዳንዶች ከፍ ያለ ሹመት አግኝተው ከአካባቢው ርቀዋል። በአሁኑ ሰአት በሶስት ቀን አንድ ቀን የቧንቧ ውሃ ማግኘት ችግር መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ህዝቡ ከ50 ዓመታት በፊት ሲጠቀምበት ወደ ነበረው የቁልሶ ወንዝ ፊቱን አዙሯል ይላሉ።
ላለፉት 50 አመታት ሲያገለግል የነበረው የውሃ መስመር ለ200 ሺ ህዝብ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰአት የህዝቡ ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል።
ስያሜዋን ከውሃ ምንጮች መብዛት ጋር በተገናኘ ያገኘችው አርባምንጭ በንጹህ ውሃ እጥረት መጠቃቷ ነዋሪዎችን ይበልጥ አስቆጥቷቸዋል።