ጥር ፲፰ ( አሥራ ስምንት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስአበባ ከተማ ትላንት ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ይፋ በተደረገው 25ኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ 50 ሺ 250 ብር ከፍተኛ ገንዘብ አንድ ተጫራች አቀረቡ፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ወረዳ 2 ውስጥ ለሚገኝ 208 ካሬሜትር ቦታ ለመግዛት ለአንድ ካሬሜትር ብር 50 ሺ 250 ብር በጠቅላላው 10 ሚሊዮን 452 ሺ ብር የሰጡት አቶ አብርሃም ህሉፍ ዓረፈዓይኔ የተባሉ ግለሰብ ናቸው፡፡ ግለሰቡ የሰጡት ገንዘብ የዙሩ ከፍተኛ ገንዘብ ሆኖ ተመዝግቦአል፡፡
በተጨማሪም በዚያው ክፍለከተማ ለአንድ ካሬሜትር 42 ሺ 227 ብር እንዲሁም 38ሺ 880 ብር የሰጡ ግለሰቦች የመረጡትን ቦታ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በአዲስአበባ መንግሥት በየጊዜው እየቆነጠረ በሚያወጣው ጨረታ የመሬት ዋጋ ጥቂት ቱጃሮች ብቻ የሚደፍሩት እየሆነ መምጣቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ከዚህ ቀደም በወጡ ጨረታዎች ለአንድ ካሬሜትር ከ350 ሺ ብር በላይ የሰጡ ግለሰቦች ጭምር የታዩ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነቱ ጤናማ ያልሆነ የግዥ ሥርዓት ሕገወጥ ገንዘብን ወደሕጋዊ ስርኣት ለማስገባት የሚፈልጉ ሙሰኞች ከጀርባ እንዳይኖሩ ሥጋት ፈጥሮአል፡፡
በሌላ በኩል ጥቂት ገንዘብ ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ በጨረታዎቹ እየተሳተፉ ወሳኝ ቦታዎችን በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም በእጃቸው ለማስገባት እየተረባረቡ መሆኑ የከተማዋ መሬት በትንንሽ ከበርቴዎች እጅ እንዲወድቅ መንገድ እየከፈተ ነው የሚሉ ቅሬታዎች እየቀረቡ ነው፡፡