ጥር ፲፰ ( አሥራ ስምንት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶም ስር በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በግፍ ተገለው ሕይወታቸውን ያጡ 14 ንፁሃን ሰላማዊ ሶማሊያዊያን ዜጎች ግድያ በገለልተኛ አካል ምርመራ ተደርጎበት እንዲጣራ ሲል ሂውማን ራይትስ ወች ጥሪ አቅርቧል።
ባለፈው ዓመት ሃምሌ ወር ላይ በሶማሊያ ባዬ ግዛት ዋርዲሌ ውስጥ የተፈፀመው ዘግናኝ የጅምላ ጭፍጨፋ ስድስት ወራት ያለፈው ሲሆን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የምርመራ ሪፖርት ካለመቅረቡም በላይ ለጉዳተኞቹ ቤተሰቦች የደም ካሳ አልተሰጠም።
በዋርዲሌ መንደር ነዋሪ የነበሩ ሰላማዊ ዜጎች ሃምሌ 17 ቀን እ.ኤ.አ.2016 በኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በሩምታ ተኩስ በግፍ ተገለዋል። በወቅቱ የአካባቢው ነዋሪዎች አንድ ሕመምተኛ ቤት ውስጥ በመገኘት ሃይማኖታዊ ፀሎት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን በግድያውም የሕመምተኛውን ቤተሰቦች ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ አዛውንቶች እና የአገር ሽማግሌዎች በጭካኔ ተገለዋል። ሂውማን ራይትስ ወች ያነጋገራቸው በስፍራው የነበሩ እማኝነታቸውን ሲሰጡ፣ በግድያው ወቅት አንድም የአልሸባብ ታጣቂዎች በአካባቢው እንዳልነበሩ ገልጸዋል።
”የአዛውንቶች፣ የሃይማኖት መምህራን እና የአገር ሽማግሌዎች ግድያ እንዳይታወቅና እንዲሸፋፈን መሞከር ወንጀል ነው። የአፍሪካ ኅብረት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ወንጀሉን የፈፀሙትን ለይተው በሕግ ተጠያቂ ማድረግ አለባቸው። ለጉዳተኛ ቤተሰቦችም ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል።” ሲሉ በአፍሪካ ቀንድ በሂውማን ራይትስ ወች የሶማሊያ የሰብዓዊ መብት አጥኚ የሆኑት ወ/ሮ ላቲቲያ ባደር ገልፀዋል።
ሃምሌ 19 ቀን እ.ኤ.አ .2016 የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን በማመን በጉዳዩ ላይ ማጣራት እንደሚያደርግ አስታውቋል። ሰላማዊ ዜጎቹ በሩምታ ተኩስ በጭካኔ መገደላቸውንና በወቅቱ ምንም ዓይነት የአልሸባብ ሚሊሻዎች አለመኖራቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቡድን አረጋግጧል። በወቅቱ በስፍራው የነበሩ ሰባት የዓይን እማኞችም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ እና የጦርነት ሕጎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይደርስ ከለላ ማድረግን ያስገድዳል። ሆኖም ግን ይህን ዓለም አቀፍ ሕግ በመጣስ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የጦር ወንጀል ፈፅመዋል። የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ጦር አባላት ከሕብረተሰቡ ጋር ያላቸውን አቅራቦት ማሻሻል እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
”የዋርዲሌው እልቅቲ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበትና ጉዳተኞቹም ካሳ ማግኘት ይገባቸዋል ሲሉ በአፍሪካ ቀንድ በሂውማን ራይትስ ወች የሶማሊያ የሰብዓዊ መብት አጥኚ የሆኑት ወ/ሮ ላቲቲያ ባደር አሳስበዋል።