ኢሳት (ጥር 17 ፥ 2009)
የደቡብ ሱዳን መንግስት የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ሳልባ-ኪር በቅርቡ በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት ሃገሪቱ ከተለያዩ ሃገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር የተካሄደ እንደሆነ ይፋ አደረገ።
በሁለቱ ሃገራት መሪዎች መካከል የተካሄደው ውይይትም የኢትዮጵያና የግብፅን ግንኙነት ያነሳ አልነበረም ሲሉ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ቃል አቀባይ የሆኑት አቴኔ ዌክ ማስታወቃቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።
የደቡቡ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልባ ኪር በቅርቡ በግብፅ ያካሄዱትን ጉብኝት ተከትሎ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሳል ባኪር ጉብኝት በኢትዮጵያ በኩል ቅሬታን እንዳሳደረ ሲዘግቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ፕሬዚደንት ሳልባኪርና የግብፅ አቻቸው አብደል ፈታህ አልሲሲ ባካሄዱት ውይይት ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት የቆየ መብት መቀጠል ባለበት ሁኔታ ዙሪያ መምከራቸውን ሲዘግብ ቆይቷል።
ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ ይፋዊ ምላሽን የሰጠው የደቡብ ሱዳን መንግስት በሁለቱ መሪዎች መካከል የተካሄደው ውይይት አንድ ሃገር ከበርካታ ሃገራት ጋር ግንኙነትን ለመፍጠርና ማጠናከር ያላትን መብት ዋቢ ያደረገ እንደነበር አመልክቷል።
የሃገሪቱ ቃል አቀባይ አቴኔ ዌክ ጉብኝቱ የደቡብ ሱዳን እና የግብፅን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነበር ቢሉም በሁለቱ ፕሬዚደንቶች መካከል ስለተካሄደው ውይይት ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሁለቱ ሃገራት በአንድ ሃገር የቅኝ አገዛዝ ውስጥ ቆይተው እንደነበር ያወሱት የደቡብ ሱዳን መንግስት ቃል አቀባይ ግንኙነት ታሪካዊ ትስስር እንዳለውም አክለው ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ አማጺያንን የመደገፍ ፍላጎት እንደሌለው አቴኔ ዌክ መናገራቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል። ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ባለፈው አመት አንደኛው ሃገር የሌላኛውን ሃገር ተቃዋሚ ቡድን ላለመደገፍ ስምምነት መፈረማቸው የሚታወስ ነው።
ሁለቱ ሃገራት የደረሱትን ይህንኑ ስምምነት ተከትሎ ኢትዮጵያ ለአንድ አመት ያህል በአዲስ አበባ ቆይታ ለነበራቸው የአማጺ ቡድኑ መሪ ሪክ ማቻር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ እገዳን ጥላለች።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለው ግኝኑነት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ማክሰኞ መግለጹን ለመረዳት ተችሏል።