በእስር ላይ የሚገኙት የዶርዜ ተወላጆች ጉዳያቸውን የሚያይ አካል መጥፋቱን ተናገሩ

ጥር ፲፮ ( አሥራ ስድስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በእስር ላይ የሚገኙት 35 የዶርዜ ብሄረሰብ ተወላጆች ላለፉት 2 ወራት ያለ ጠያቂ በአርባምንጭ እስር ቤት ውስጥ እየተሰቃዩ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ጉዳያቸው በፍጥነት ታይቶ ፍርድ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ግለሰቦቹ የተያዙት የማንነት ጥያቄ አነስታችሁዋል በሚል ነው። የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ጉዳያቸውን እስከ ጠ/ሚኒስትሩ ድረስ ቢያቀርቡም መልስ የሚሰጣቸው አካል አላገኙም። ይልቁንም የብሄረሰቡ ዋና ዋና ወኪሎች የሚባሉ ሰዎችን እያሳደዱ ማሰር መቀጠሉን የብሄረሰቡ ተወካዮች ለኢሳት ተናግረዋል።
ገዢው ፓርቲ በጋሞና ዶርዜ ህዝብ መካከል ልዩነት በመዝራትና በመከፋፈል ለማጋጨት እየሰራ ነው በማለት የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። “ ሲዋርድ ሲዋረድ የመጣው አብሮ የመኖር እሴት እየጠፋ” መሆኑን የሚናጉት ነዋሪዎች፣ አሁንም ችግሩን ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ችግሩ እንዲባባስ የተለያዩ ቅስቀሳዎች እየተደረጉ በመሆኑ በአካባቢው ግጭት ይነሳል የሚል ስጋት አላቸው።
የአገር ሽማግሌዎች ራሳቸውን በማደራጀት በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር የተቻላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውም ታውቋል። በእስር ላይ የሚገኙት የዶርዜ ብሄረሰብ አባላት ከእስር ካልተፈቱ ችግሩን እንደሚያወሳስበው የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ባለፈው ዓመት በደቡብ ኦሞ ዞን በአርቦሬና ሃመር ህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የተደረገው ጥረት በአገር ሽማግሌዎች ጥረት እንዲበርድ ተደርጓል።