የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ተጨማሪ ሃይል ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲገባ ወሰነ

ጥር ፲፮ ( አሥራ ስድስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ሱዳን የቀጠለው ግጭት አሳስቦኛል ያለው ድርጅቱ፣ በአብዛኛው የአገሪቱ ቦታዎች የሰብአዊ እርዳታ ሊደርስ እንዳልቻለ ገልጿል።
የጸጥታው ምክር ቤት በዝግ ባደረገው ምክክር ተጨማሪ ሃይል ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲላክ መወሰኑን የድርጅቱ የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ስዊድናዊው ኦሎፍ ስኮግ ተናግረዋል። ሰኮግ የደቡብ ሱዳን መንግስት ከጸጥታው ምክርቤት ጋር እንዲተባበርና የድርጅቱ የሰላም አስከባሪ ሃይል በፍጥነት ወደ አገሪቱ እንዲገባ እንዲፈቅድ ጠይቀዋል።
ደቡብ ሱዳን የአገሪቱን መረጋጋት በመግለጽ ተጨማሪ 4 ሺ የተመድ ጦር እንደማትቀበል አስታውቃ ነበር። በሰላም አስከባሪ ስም ወደ አገሪቱ የሚገቡት የኢትዮጵያ እና የሩዋንዳ ጦር ሳይሆን እንደማይቀር ደይሊ ሜል ዘግቧል።
በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል አለመግባባት መፈጠሩን የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው። ኢትዮጵያ በተመድ የሰላም አስከባሪ ስም ሰራዊቷ በደቡብና ሰሜን ሱዳን ይገኛል። ሰራዊት በሰላም አስከባሪ ስም መላክ ለገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ከፍተኛ የሃብት ምንጭ እንደሆናቸው በተመድ ሰላም አስከባሪ ስም ተልከው አገልግሎት የሰጡ ወታደሮች ይገልጻሉ።