ለአለም ጤና ድርጅት ቀጣይ ዳይሬክተር ለመሆን ከቀረቡ ስድስት ተወዳዳሪዎች የመጨረሻ ሶስቱን ለመምረጥ የመለየት ስራ ተጀመረ

ኢሳት(ጥር 16 ፥ 2009)

የአለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያን ጨምሮ የተቋሙ ቀጣይ ዋና ዳይሬክተር ለመሆን ከቀረቡ ስድስት የተለያዩ ሃገራት ተወዳዳሪዎች መካከል የመጨረሻ ሶስቱን የመምረጥና የመለየት ስራ ተጀመረ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ የጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታኒያ፣ ፓኪስታንና የሃንጋሪ ተወዳዳሪዎች በስዊዘርላንድ መዲና ጀኔቫ ለዚሁ ምርጫ መሰባሰባቸውን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

ከአለም ጤና ድርጅት አባል ሃገራት መካከል በድርጅቱ ከሶስት አመት በላይ በቦርድ አባልነት የተመረጡ የ36 አገራት ተወካዮች ድምፅ በመስጠት ከስድስቱ ተወዳዳሪዎች መካከል አምስቱ ታውቀዋል።

ከአለም ጤና ድርጅት አባል ሃገራት መካከል በድርጅቱ ሶስት አመት በላይ የቦርድ አባልነት የተመረጡ የ36 አገራት ተወካዮች ድምፅ በመስጠት ከስድስቱ ተወዳዳሪዎች መካከል አምስቱን ማክሰኞ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አምስቱ ተወዳዳሪዎች ደግሞ ረቡዕ ለአንድ ሰዓት ያህል የሚቆይ ዝግ ቃለመጠይቅ ከተደረገላቸው በኋላ የመጨረሻዎቹ ሶስቱ ተወዳዳሪዎች በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚለዩ የአለም ጤና ድርጅት አመልክቷል።

ይሁንና የቦርድ አባል ሃገራት የሆኑት ካናዳ ኮሎምቢያ ተወዳዳሪዎቹን ለመለየት በዝግ የሚካሄደው ቃለመጠይቅ ለህዝብ ክፍት እንዲሆነ ጥያቄን ቢያቀርቡም ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን ለመረዳት ተችሏል።

የ34 ሃገራት ተወካዮች የበላይ የቦርድ አባላት በሚሰጡት ድምፅ ለመጨረሻ ዙር የሚቀርቡት ሶስቱ ተወዳዳሪዎች የድርጅቱ አባል ሃገራት የፊታችን ግንቦት ወር በሚያካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ድምፅ ተሰጥቶባቸው ቀጣዩ የአለም ጤና ድርጅት ሃላፊ እንደሚታወቅ ተመልክቷል።

አሜሪካ ከ34 የአለም ጤና ድርጅት የበላይ ቦርድ አባል ሃገራት መካከል አንዷ ብትሆንም በአሁኑ ወቅት ውክልና ይዘው የሚገኙት የሃገሪቱ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ሃላፊ ዶ/ር ቶም ፍሬደን በፕሬዚደንት ትራም አስተዳደር ቀጣይ እንደማይሆኑ ተነግሯል።

ይሁንና ተሰናባቹ ተወካይ በድምፅ መስጠቱ ሂደት ተሳታፊ እንደሚሆኑና ድምጻቸውን ለማን መስጠት እንዳለባቸው ይፋ ማድረግ እንደማይፈልጉ በጤናና መድሃኒቶች ዙሪያ ለሚሰራው ስታትኒውስ (statnews.com) መጽሄት አስታውቋል።

ለአለም ጤና ድርጅት ሃላፊነት ተወዳዳሪ ሆነው ከቀረቡት መካከል የህክምና ባለሙያ ያልሆኑትና በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ድጋፍን ያገኙት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአለም ጤና ድርጅት ሃገራት ድምፅ ለማግኘት ቅስቀሳ ሲያካሄዱ መቆየታቸውም ታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የአለም ጤና ድርጅት የቦርድ አባል ሃገራት ተወካዮች ጋር ሰኞ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ማካሄዱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የአለም የጤና ድርጅት የቦርድ አባላት በቀጣዩ አምስት ቀናቶች በሚኖራቸው ልዩ ስብሰባ የመጨረሻ ሶስቱ ተወዳዳሪዎች ለህዝቡ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በአሁኑ ወቅት ድርጅቱን በመምራት ላይ ያሉት ቻይናዊቷ ዶ/ር ማርጋሬት ቻን ለሁለተኛ ጊዜ በመመረጥ የጤና ተቋሙን ለ10 አመት በማገልገል ላይ ሲሆኑ የስልጣን ዘመናቸው የፊታችን ሰኔ ወር እንደሚያበቃ ለመረዳት ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ዛሬ ማክሰኞ ከቀረቡት ስድስት ተፎካካሪዎች መካከል የሃንጋሪው ተወካይ ሚካሎስ ዘግላክ ከውድድሩ መሰናበታቸውን የአለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የቦርድ ጸሃፊ የሆኑት ሬይ ቡሲቲል የተቀሩት አምስት ተወዳዳሪዎች ከነገ ረቡዕ ጀምሮ ቃለመጠይቅ ከተካሄደላቸው በኋላ ሶስቱ ተለይተው እንደሚታወቁ ተገልጿል።