ኢሳት (ጥር 15 ፥ 2009)
በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን አዲስ የድርቅ አደጋ ተከትሎ ወደ 600 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ተገለጸ።
በሶማሌ ክልል ስር በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ብቻ በምግብና ውሃ አቅርቦት ችግር 442 ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን፣ 183 ሺ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው መቅረታቸውን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰኞ ይፋ አድርጓል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል በቦረናና ጉጂ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች 141 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው 47 ሺ አካባቢ የሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጣቸው በሃገር ውስ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ አፋርና፣ ደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በተከሰተ አዲስ የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚፈልጉ ማስታወቁ ይታወሳል።
በድርቁ ምክንያት ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዲስ የተከሰተው የድርቅ አደጋ እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑን በማስታወቅ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ርብርብ እንዲያደርግ ከቀናት በፊት ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። በአራቱ ክልሎች ተከስቶ ያለውን ይህንኑ የድርቅ አደጋ ለመካላከል ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግም ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።
ድርቁ በተለያዩ ወረዳዎች እያደረሰ ያለውን ጉዳት መጨመርን ተከትሎ የሚዘጉ ትምህርት ቤቶችና ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች በመጨመር ላይ ሲሆኑ በአፋርና የደቡብ ክልሎችም ተመሳሳይ ችግር መኖሩ ታውቋል።
ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች ተከስቶ በነበረው የድርቅ አደጋ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የነበረ ሲሆን፣ 10.2 ሚሊዮን ሰዎችም ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ መጋለጣቸው የሚታወስ ነው።
ይኸው የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ሳያገኝ አዲስ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገልጻል።
መንግስት በበኩሉ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድርቁን ለመከላከል እየተደረገ ላለው ጥረት ድጋፍን እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል። አዲስ የተከሰተው የድቅ አደጋ እስከተያዘው አመት መጨምረሻ ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችልም ተተንብዩአል።