ኢሳት (ጥር 12: 2009)
በኢትዮጵያ ታውጆ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈለገውን ሰላም ባለማምጣቱ፣ ለተጨማሪ ወራት ሊራዘም እንደሚችል አንድ በደህንነት ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚይቀርብ ጋዜጣ አስታወቀ። ከአንድ አመት በላይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በሃገሪቱ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት ለውጥ እንዳላመጣ ጋዜጣው ዘግቧል።
አፍሪካ ኮንፊደንሻል የተባለው ይኸው ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ ቀውስና ህዝባዊ ተቃውሞ መሻሻል አለማሳየቱን ገልጾ፣ ተቃዋሚ ሃይሎችም በተበታተነ መልኩ እንደሚገኙ አመልክቷል።
በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞው ተከትሎ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ክፉኛ የተጎዳ መሆኑን የገለጸው አፍሪካ ኮንፊደንሻል፣ ወቅቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ጉድለት የታየበት እንደሆነ አትቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቱሪስቶች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተዕፅኞ መፍጠሩ አመልክቷል።
አፍሪካ ኮንፊደንሻል የኢትዮጵያ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ እየመለስኩ ነው፣ ማሻሻያዎችንም እየወሰድኩ ነው ቢልም፣ እስካሁን ድረስ የፖለቲካ ቀውሱ መሻሻል እንዳላሳየ በድረገጹ አስፍሯል።
ባለፈው ጥቅምት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴዎችን ሽባ ያደረገ መሆኑንም ያተተው ጋዜጣው፣ መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድ በተቃርኖ የተሞላ እንደሆነ አመልክቷል። መንግስት በአንድ በኩል ማሻሻያ እያደረግኩ ነው ቢልም፣ በሌላ በኩል በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ጫና እና አፈና እያደረገ እንደሆነ ገልጿል። አሁን በስልጣን ላይ ያለው የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ ለዲሞክራሲ መዳበርና ተጠያቂነት እንዲሰፍን እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ የማያደርግ መሆኑን አመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተነሱ ተቃውሞዎችን ለማዳፈን ቀንና ሌት እየሰራ እንደሆነ የገለጸው አፍሪካ ኮንፊደንሻል፣ ህወሃት/ኢህአዴግ የተወሰኑ የመንግስት ባለስልጣናትን በሙስና ሰበብ በማሰር በፍርድ ቤት ድራማ ሊሰራ እንደሚችል አመልክቷል። ሆኖም ግን እየተጓዘበት ካለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ አካሄድ ለውጥ ሳያደርግ እንደሚቀጥል ገልጿል።