የደቡብ ሱዳን አማጺ ቡድን አመራሮች በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ታወቀ

ኢሳት (ጥር 11 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር የአማጺ ቡድንን ላለመደገፍ ስምምነት ብትፈራረምም፣ አሁንም ድረስ የሃገሪቱ አማጺ ቡድን አመራሮች በአዲስ አበባ መሆናቸው ተገለጸ።

የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ ምክትል ወታደራዊ ቃል አቀባይ የሆኑት ዲክሰን ጋትሉአክ (Dickson Gatluak) የቡድኑ አዛዥ ሪክ ማቻር በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ቢሆኑም እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ለቪኦኤ የእንግሊዝኛው ክፍል አስታውቋል።

በጎረቤት ሱዳን የሚገኙ የአማጺ ቡድኑ አባላት መኮበብላቸውን አስመልክቶ የተጠየቁ ቃል አቀባዩ ከካርቱም ወደ ጁባ ገብተዋል የተባሉ አመራሮች ከአማጺ ቡድኑ ጋር ግንኙነት የሌላቸው መሆኑን ለዜና ጣቢያው በሰጡት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በደቡብ ሱዳን ጁባ የሚገኝ አንድም የአማጺ ቡድኑ አመራር አለመኖሩንና እርሳቸውን ጨምሮ በሪክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን አመራሮች በአዲስ አበባ እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።

ከወራት በፊት የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት አንደኛው ሃገር የሌላኛውን ሃገር አማጺ ቡድንና ተቃዋሚ ድርጅት ላለመደገፍ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

የስምምነቱ መፈራረም ተከትሎም ኢትዮጵያ የአማጺ ቡድኑ መሪና ለአንድ አመት ያህል በአዲስ አበባ ተቀምጠው የነበሩት ሪክ ማቻር ወደ ሃገሪቱ እንዳይገቡ እገዳን ጥላ ትገኛለች።

ይሁንና አሁንም ድረስ ቁጥራቸው ያልተገለጸ የሪክ ማቻር አማጺ ቡድን አመራሮች በአዲስ አበባ የሚገኙ ሲሆን፣ የቡድኑ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ዲክሰን ጋትሉአክ አመራሮቹ የተፈረሙ ስምምነቶች ተግባራዊ እስከሚሆኑ ድረስ በአዲስ አበባ እንደሚቆዩ ይፋ አድርገዋል።

የአማጺ ቡድኑና የፕሬዚደንት ሳልባኪር መንግስት ባለፈው አመት የብሄራዊ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ስምምነት መድረሳቸው የሚታወስ ነው።

የስምምነቱ መድረስን ተከትሎ መቀመጫቸው በአዲስ አበባ አድርገው ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ድርድርን ሲያደርጉ የነበሩት ሪክ ማቻር የምክትል ፕሬዚደንትነት ስልጣን ተሰጥቷቸው ወደ ጁባ እንዲጓዙ ተደርጓል።

ይሁንና ሁለቱ ወገኖች ዳግም ወደ ግጭት መግባታቸውን ተከትሎ ማቻር ከሃገሪቱ የተሰደዱ ሲሆን ሌሎች ከፍተኛ የቡድኑ አመራሮች ግን አሁንም ድረስ በአዲስ አበባ መሆናቸው ተመልክቷል።

የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚደንት ሳልባኪር በቅርቡ ወደ ግብጽ በመጓዝ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ አድርገውታል የተባለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር አዲስ አለመግባባት ማስነሳቱም ይነገራል።

የኢትዮጵያም ሆነ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ ይፋዊ መግለጫን ባይሰጡም በአዲስ አበባ የሚገኙት የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ከግብፅ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ኢትዮጵያን ለመጉዳት የታሰበ አይደለም ሲሉ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማስተባበያ ሰጥተዋል።