ኢሳት (ጥር 11 ፥ 2009)
የደቡብ ሱዳን መንግስት በቅርቡ ከግብፅ ጋር የደረሰውን የአባይ ወንዝ ስምምነት አስመልክቶ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ማብራሪያ እንደማይኖር የሃገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ገለጸ።
ደቡብ ሱዳን ጥቅሟን ለማስጠበቅ በምታደርገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያንም ሆነ ማንንም አገር አትፈራም ሲሉ የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሃላፊ ለመገኛኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ሃላፊው አቲ ዲንግ በአዲስ አበባ የሚገኙት የሃገሪቱ አምባሳደር በጉዳዩ ዙሪያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ መደረጉንም ለጋዜጠኞች እንደገለጹ ሚያሚሌፒዲያ የተሰኘ የሃገሪቱ የመገኛኛ ተቋም ዘግቧል።
በካይሮ ያልተጠበቀ ጉብኝት አድርገዋል የተባሉት ፕሬዚደንት ሳልባኪር ከግብፅ አቻቸው አብደል ፈታህ አልሲሲ ጋር በመገኛኘት ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት የቆየ መብት መቀጠል በሚኖርበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውና ስምምነት መድረሳቸው ይፋ ተደርጓል።
ይሁንና ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት ይኸው ስምምነት በኢትዮጵያ በኩል ተቃውሞ ማስነሳቱን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ አዲስ አበባ የሚገኙት የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒታ-ሞርጋ ማክሰኞ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው ማስተባበያን ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ ሃገራቸው ከግብፅ ጋር የደረሰችው ስምምነት ከግብፅ ኢትዮጵያን የሚጎዳ አይደለም በማለት ማስተባበያን ቢሰጡም የሃገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላት ይፋ አድርጓል።
ደቡብ ሱዳን ጥቅሟን በማስጠበቋ ኢትዮጵያ ልታስፈራራን አትችልም ሲሉ የገለጹት አቴም ዴንግ፣ ከሃገሪቱ የተለያዩ ድጋፎች ከምታደርገው ግብፅ ጋር ያለው ግንኙነት መቼም ቢሆን አይቋረጥም ሲሉ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ግብፅ ለደቡብ ሱዳን በመስኖ፣ በደህንነትና በሌሎች ተጓዳኝ ዘርፎች ለሃገሪቱ ድጋፍን እየሰጠች እንደሆነ ሃላፊው ለመገኛኛ ብዙሃን መግለጻቸውን የዜና ተቋሙ በሪፖርቱ አስነብቧል።
“ደቡብ ሱዳን ከግብጽ ጋር በአባይ ወንዝ ዙሪያም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ያላት ትብብር እንዲቋረጥ ማንም ሊጠይቀን አይገባም” ሲሉ ዴን አክለው ተናገረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የግብጽ እንቅስቃሴ በጥርጣሪ ቢመለከትም በተመሳሳይ መልኩ ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያ የሃገሪቱ አማጺ ቡድንን በእጅ አዙር ትደግፋለች በማለት ጥርጣሬ እንዳላት የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ። በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰው ይኸው አለመግባባት እየሰፋ ሊሄድ እንደሚችልም ተነግሯል።
ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን መንግስትና በሪክ ማቻር የሚመራውን አማጺ ቡድን በማደራደር የሰላም ስምምነት እንዲደርሱ ብታደርግም ከፍተኛ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ኢትዮጵያ ለአማጺ ቡድኑ ድጋፍ ታደርጋለች ሲሉ በገሃድ ቅሬታን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።