ጥር ፲፩ ( አሥራ አንድ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በውጭ ምንዛሬ እጥረት በሚል ሰበብ ከተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንና እህት ኩባንያዎች የተሰናበቱት ከ500 በላይ ሰራተኞች ከስራቸው የተቀነሱት በብሄራቸው ምክንያት መሆኑን ተናገረዋል።
የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንና እህት ኩባንያዎች እንደ አብዛኛዎቹ የሃገሪቱ ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር እንደገጠማቸው ቢታወቅም ከስራቸው የተቀነሱት ሰራተኞች ማንነት ሲጣራ ሙሉ በሙሉ የአማራና የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች መሆናቸው ቅነሳው ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው ብለው እንዲያስቡ እንዳደረጋቸው የሰራተኞች ተወካዮች ገልጸዋል።
ሰራተኛውን ወክለው ጥቅማጥቅማቸውን ለማስከበር ከሚንቀሳቀሱት ተወካዮች መካከል አንዱ ለኢሳት እንደተናገረው ስራቸውን ያጡት የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ ነው። ቅሬታ አቅራቢዎች ድርጅቱ የህወሃት ሰዎች ንብረት በመሆኑ የብሄር ማንነታቸውን መሠረት ባደረገ መልኩ ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በውጭ ምንዛሬ እጥረት በሚል ሰበብ ከ500 በላይ ሰራተኞች ቢያሰነበትም ተገቢውን ጥቅማጥቅምና ስርዓቱን የጠበቀ ስንብት በለማድረጉ መቸገራቸውንም ተወካዩ ተናግዋል፡፡
የድርጅቱ ተሰናባች ሰራተኞች ድንገት ከስራ መቀነሳቸው ዱብ ዕዳ እንደሆነባቸው ህዳር ወር ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተናገሩት በተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ውስጥ ለአምስት ዓመታት ሲሰሩ እንደቆዩ የገለፁት የግንባታ ባለሙያ፤ “በቅርቡ አተረፍኩ ብሎ ጉርሻና ማበረታቻ የሰጠ ድርጅት ስራ አጣሁ ብሎ ይሄን ሁሉ ሰራተኛ መቀነሱ አስደንጋጭ ነው” በማለት መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
ሌላው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ተሰናባች በበኩላቸው “ድርጅቱ ወደ መንገድ ግንባታ ለመግባት በ500 ሚሊዮን ብር ማሽነሪዎችን ካስገባ አራት ወራት እንኳን እንዳልሞላው ገልፀው፤የህንፃ ግንባታና የመንገድ ግንባታ መጠነኛ ልዩነት ቢኖራቸው እንኳን በስልጠና ሰራተኛውን ወደዚያው ማዞር ይቻል እንደነበር መግለጻቸውን ጋዜጣው አስነብቧል፡፡
ጋዜጣው ሰራተኞቹ ባነሷቸው ነጥቦች ዙሪያ ጥያቄ ያቀረበላቸው ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ የ500 ሚሊዮን ብር ማሽነሪዎች ማስገባታቸውን አምነው መሳሪያዎቹ ከሁለትና ከሶስት የመንገድ መስሪያ ዶዘሮች በስተቀር 99 በመቶው የህንፃ ግንባታ ማሽነሪዎች መሆናቸውን መግለጻቸው ዘግቧል።
ሌላዋ የድርጅቱ ተሰናባች ለአዲስ አድማስ በሰጠችው አስተያየት፣ድርጅቱ አራት ኪሎ ሳይት ላይ በጀመረው አዲስ ግንባታ አዳዲስ ሰራተኞችን እየቀጠረ ባለበት ሁኔታ ነባሮቹንና በድርጅቱ ውስጥ ልምድ ያዳበሩትን መቀነስ ተገቢ አለመሆኑን ተናግራለች፡፡
በአዲስ አበባ ለረዥም ጊዜ ነዋሪ የነበሩና በተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ውስጥ የሰሩት የአማራ ክልል ተወላጅ ለኢሳት እንደገለጹት የተቀነሱት ሰራተኞች በማንነታቸው ከመወገዳቸውም በላይ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅማጥቅም ድርጅቱ ሊከፍላቸው ባለመቻሉ አብዛኛው ሰራተኞች እየተቸገሩ ነው፡፡
በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች ህዝባዊ አመጾች ከተነሱ በሁዋላ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው የብሄር ልዩነት እየሰፋ መሄዱን፣ በህወሃት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ኩባንያ ስራ አስኪያጆች የሌሎች ብሄር ተወላጆችን በጥርጣሬ ማየት መጀመራቸውን ለኢሳት የሚደርሱ ሪፖርቶች ያመለክታሉ ። የህወሃት ንብረት የነበሩ አንዳንድ ፋብሪካዎች ከህዝባዊ አመጹ ጋር በተያያዘ መውደማቸው ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የዶላር እጥረት መከሰቱ እውን ቢሆንም፣ ከተክለብርሃን አምባዬ በስተቀር በግንባታው ዘርፍ ስማቸው ደጋግሞ የሚጠሩ ኩባንያዎች ሰራተኞችን አልቀነሱም።
በጉዳዩ ዙሪያ የተክለብርሃን አንባዬን ባለቤት ወይም አመራሮች ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም።
ተክለብርሃን አምባዬ የኮንስትራክሽን ኩባንያ እና አፍረጺዮን የኮንስትራክሽን ድርጅት በርካታ የመንግስት የግንባታ ፕሮጀክቶችን ወስደው የሚሰሩ፣ ህወሃት ከጀርባ ሆኖ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ድርጅቶች መሆናቸውን አንድ ሰማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የግንባታ ባለሙያ ይናገራሉ።