ጥር ፲፩ ( አሥራ አንድ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት በምእራብ ጎጃሟ የፍኖተሰላም ከተማ በርካታ የቅስቀሳ በራሪ ወረቀቶች ተበትነው አድረዋል። ይህን ተከትሎም ወታደሮች በብዛት ወደ ከተማዋ ገብተዋል። በወረቀቱ ላይ “ ሞት ለወያኔ” የሚል መፈክር የሰፈረ ሲሆን፣ 9 ነጥቦችም ተዘርዝረው ቀርበዋል። የአርሶአደሩ መሬት አልባነትና የከተማው ነዋሪ ቤት አልባነት እንዲቆም እንዲሁም በ1 ለ 5 የጥርነፋ ስልት አገዛዙ እርስ በርስ ህዝቡን እያጋጨ በመሆኑ ወጣቱ ይህን ተገንዝቦ ለመብቱ እንዲነሳ የተበተነው ወረቀት ጥሪ ያቀርባል። ወረቀቱን በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የነጻነት ሃይሎች መበተናቸው ገልጸዋል።
በሌላ ዜና የፍኖተሰላም ከተማ አጎራባች በሆነቸው በቡሬ ከተማ አንድ ነዋሪ መሳሪያውን ሊነጥቁ ከመጡት የፌደራል ፖሊሶች መካከል አንዱን ገድሎ ሌላውን ማቁሰሉን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ሲሆን፣ ሁለት የፌደራል ፖሊሶች የጦር መሳሪያ ለመውሰድ ወደ አንድ ግለሰብ ቤት ሲገቡ ግለሰቡ መሳሪያውን ላለማስረከብ ተኩስ በመክፈቱ አንዱ ፖሊስ ወዲያውኑ ህይወቱ ሲያልፍ ሌላው ፖሊስ ደግሞ ቆስሎ ሆስፒታል ገብቷል። ግለሰቡም ደረቱ እና አንገቱ አካባቢ ተመትቶ በአሁኑ ሰአት ፍኖተሰላም ሆስፒታል በመታከም ላይ ይገኛል።
ከፍኖተሰላም ዜና ሳንወጣ አንድ የደንበጫ ከተማ ተወላጅ የሆነ መምህር ጫካ ውስጥ ተገድሎ መገኘቱን ለማወቅ ተችሎአል። ሆዳንሽ በሚባል ጎጥም እንዲሁ አንድ ሌላ ግለሰብ ተገድሎ መገኘቱን ምንጮች ገልጸዋል።