ኢሳት (ጥር 10 ፥ 2009)
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቂሊንጦ እስር ቤት የእሳት ቃጠሎ አደጋ እንዲደርስ አድርገዋል ተብለው የተከሰሱ እስረኛ ተከሳሾች የክስ ሂደታቸው በዝግ ችሎት እንዲታይ ጠየቀ።
ጥያቄውን ለፍርድ ቤት ያቀረበው ጠቅላይ አቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ ምስክርነት መስጠት የጀመሩ ግለሰቦች ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው ሲል ቅሬታውን እንዳቀረበ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
ባለፈው አመት ነሃሴ ወር በቂሊንጦ እስር ቤት ደርሶ በነበረው የእሳት አደጋ ከ20 የሚበልጡ እስረኞች መሞታቸውና 15 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት መውደሙ ተገልጿል።
የቂሊንጦ እስር ቤት ለእሳቱ መንስዔ በእስር ቤቱ የሚገኙ 38 ተከሳሾች ናቸው ሲል መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በእነዚሁ እስረኞች ላይ ክሱን በቅርቡ መመሰረቱ ይታወሳል።
ይሁንና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለችሎት ማቅረብ የጀመራቸው የሰው ምስክሮች ዛቻና ማስፈራራት እየደረሰባቸው ነው ሲሉ ጉዳዩ በዝግ ችሎት እንዲታይ ለፍርድ ቤት ጥያቄን ማቅረቡ ታውቋል።
የቀረበውን ይህንኑ ጥያቄ ተከትሎ ተከሳሾችና የተከሳሽ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ ጥያቄን ለማቅረብ ቢሞክሩም ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን “አንቀበልም፣ በጽ/ቤት በኩል አቅርቡ” የሚል መልስ መስጠቱ ጋዜጣው በዘገባው አስነብቧል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ እስረኛ ተከሳሾችን ለእሳት ቃጠሎና ለሞቱ ሰዎች ተጠያቂ ናቸው ቢልም፣ የአይን እማኞችና የእስር ቤቱ አንድ ጠባቂ በእለቱ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በከፈቱት የተኩስ ዕርምጃ በርካታ እስረኞች መሞታቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ ቆይተዋል።
የእስር ቤቱ አስተዳደር በበኩሉ በእሳት ቃጠሎው አደጋ እስረኞቹ በጢስ ታፍነውና ተረጋግጠው እንደሞቱ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።